ኢየሱስ በቤተመቅደስ ውስጥ
23 ቁጥሮች2አማርኛሉቃ 2:41-52
41ወላጆቹም በያመቱ በፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ነበር።
42የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ፥ እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤
43ቀኖቹንም ከፈጸሙ በኋላ፥ ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር።
44ከመንገደኞች ጋር የነበረ ስለ መሰላቸው የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፥ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም ዘንድ ፈለጉት፤
45ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
46ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቅደስ አገኙት፤
47የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ።
48ባዩትም ጊዜ ተገረሙ፥ እናቱም፦ “ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን” አለችው።
49እርሱም፦ “ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው።
50እነርሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም።
51ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር።
52ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።
ሉቃ 3:7-17
7ስለዚህ ከእርሱ ሊጠመቁ ለወጡት ሕዝብ እንዲህ ይላቸው ነበር፦ “እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?
8እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም፦ አብርሃም አባት አለን፡ ማለትን አትጀምሩ፤ ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር እንዲችል፡ እላችኋለሁና።
9አሁንስ ምሳር ደግሞ በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።”
10ሕዝቡም፦ “እንግዲህ ምን እናድርግ?” ብለው ይጠይቁት ነበር።
11መልሶም፦ “ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል፥ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ፡” ይል ነበር።
12ቀራጮችም ደግሞ ሊጠመቁ መጥተው፦ “መምህር ሆይ፥ ምን እናድርግ?” አሉት።
13“ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ፡” አላቸው።
14ጭፍሮችም ደግሞ፦ “እኛ ደግሞ ምን እናድርግ?” ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም፦ “በማንም ግፍ አትሥሩ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፥ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ፡” አላቸው።
15ሕዝቡም ሲጠብቁ ሳሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ፦ “ይህ ክርስቶስ ይሆንን?” ብለው ሲያስቡ ነበር፥
16ዮሐንስ መልሶ፦ “እኔስ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤
17መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል፡” አላቸው።