ትንቢተ ሶፎንያስ 3

AMHEVGአማርኛ20 ጥቅሶች3:54 አዳምጥ
አዳምጥ 3:54 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ለዓመፀኛይቱና ለረከሰች ለአስጨናቂይቱም ከተማ ወዮላት!

2ድምፅን አልሰማችም፥ ተግሣጽንም አልተቀበለችም፤ በእግዚአብሔርም አልታመነችም፥ ወደ አምላክዋም አልቀረበችም።

3በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ እንደሚያገሡ አንበሶች ናቸው፤ ፈራጆችዋም እስከ ነገ ድረስ ምንም እንደማያስቀሩ እንደ ማታ ተኵላዎች ናቸው።

4ነቢያቶችዋ ቅሌታሞችና ተንኰለኞች ሰዎች ናቸው፤ ካህናቶችዋም መቅደሱን አርክሰዋል፥ በሕግም ላይ ግፍ ሠርተዋል።

5እግዚአብሔር በውስጥዋ ጻድቅ ነው፤ ክፋትን አያደርግም፤ ፍርዱን በየማለዳው ወደ ብርሃን ያወጣል፥ ሳያወጣውም አይቀርም፤ ዓመፀኛው ግን እፍረትን አያውቅም።

6አሕዛብን አጥፍቻለሁ፤ ግንቦቻቸው ሁሉ ፈርሰዋል፤ መንገዳቸውን ማንም እንዳያልፍባት ምድረ በዳ አድርጌአለሁ፥ ከተሞቻቸውም ማንም እንዳይኖርባቸው፥ አንድስ እንኳ እንዳይቀመጥባቸው ፈርሰዋል።

7እኔም፦ “ይፈሩኛል፥ ተግሣጽንም ይቀበላሉ፤ ካዘዝኋትም ሁሉ ከዓይንዋ ምንም አይጠፋም፡” ብዬ ነበር፤ እነርሱ ግን በማለዳ ተነሥተው ድርጊታቸውን ሁሉ አረከሱ።

8መዓቴንና የቍጣዬን ትኵሳት ሁሉ አፈስስባቸው ዘንድ ፍርዴ አሕዛብን ለመሰብሰብ፥ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነውና፥ ምድርም ሁሉ በቅንዓቴ እሳት ትበላለችና ስለዚህ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፥ ይላል እግዚአብሔር።

9በዚያን ጊዜም አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሐን ልሳን እመልስላቸዋለሁ።

10ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ፥ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፥ ቍርባኔን ያመጡልኛል።

11በዚያን ጊዜ እየታበዩ የሚፎክሩትን ከመካከልሽ አወጣለሁና፥ አንቺም በቅዱስ ተራራዬ ዳግመኛ አትኰሪምና በዚያ ቀን በእኔ ላይ ተላልፈሽ በሠራሽው ሥራ ሁሉ አትፍሪም።

12በመካከልሽም የዋህና ትሑት ሕዝብን አስቀራለሁ፤ በእግዚአብሔርም ስም ይታመናሉ።

13የእስራኤል ቅሬታ ኃጢአትን አይሠሩም፥ ሐሰትንም አይናገሩም፥ በአፋቸውም ውስጥ ተንኰለኛ ምላስ አይገኝም፤ እነርሱም ይሰማራሉ፥ ይመሰጉማል፥ የሚያስፈራቸውም የለም።

14የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፥ እልል በል፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ በፍጹም ልብሽ ሐሤት አድርጊ ደስም ይበልሽ።

15እግዚአብሔር ፍርድሽን አስወግዶአል፥ ጠላትሽንም ጥሎአል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከልሽ አለ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አታዪም።

16በዚያን ቀን ለኢየሩሳሌም፦ “ጽዮን ሆይ፥ አትፍሪ፥ እጆችሽም አይዛሉ።

17አምላክሽ እግዚአብሔር በመካከልሽ ታዳጊ ኃያል ነው፤ በደስታ በአንቺ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩም ያርፋል፥ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል፡” ይባላል።

18“ከጉባኤው ርቀው የሚያዝኑትን፥ ከአንቺም የሆኑትን እሰበስባለሁ፤ ስድብ እንደ ሸክም ከብዶባቸው ነበር።

19በዚያ ዘመን እነሆ፥ ባስጨነቁሽ ሁሉ ላይ አደርግባቸዋለሁ፤ አንካሳይቱንም አድናለሁ፥ የተጣለችውንም እሰበስባታለሁ፤ ባፈሩባትም ምድር ሁሉ ላይ ለምስጋናና ለከበረ ስም አደርጋቸዋለሁ።

20በዚያ ዘመን አስገባችኋለሁ፥ በዚያም ዘመን እሰበስባችኋለሁ፤ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር።

ማብራሪያ

3:1-7 ቅዱሱ አምላክ ኃጢአትን በእርሱ ዘንድ ይበልጥ ቅርብ በሆኑት ላይ ከሁሉ በላይ ይጠላል። ኃጢአተኛነት አሁንና ወደፊትም የሰቆቃ ሁኔታ ነው። ሆኖም የእግዚአብሔር መገኘት ምልክቶች፣ ፈቃዱን የማወቅም የተሟሉ ጥቅሞች፣ እንዲሁም እርሱን እንዲያደርጉት እጅግ በርትተው የሚገፉ ምክንያቶች እያሏቸው፤ አሁንም በአለመታዘዝ ጸንተዋል። የሚያሳዝነው ግን፣ ሰዎች መልካምን ከሚያደርጉ አማኞች ይልቅ ክፉን በመሥራት ብዙ ጊዜ ይበልጥ ቅንዓተኛ ናቸው።

3:8-13 የወንጌል ስብከት ትንቢት ተነግሮለት ነበር፣ በአይሁድ ሕዝብ ላይም በቀል በሚፈጸምበት ጊዜ። የወንጌል የማንጻት ትምህርቶች፣ ወይም የጌታ የጸጋው ንጹሕ ቋንቋ፣ ሰዎችን የትሕትናን፣ የንስሓንና የእምነትን ቋንቋ እንዲናገሩ ያስተምር ነበር። በዕለት ተዕለት ንግግር ንጽሕናና እግዚአብሔርን መምሰል መልካም ነው። በመጨረሻው ዘመን የቤተ ክርስቲያን ንጹሕና ደስተኛ ሁኔታ የታሰበበት ይመስላል። ጌታ ትምክህትን ያጠፋል፤ ሰዎችንም ከጌታ ከኢየሱስ በቀር የሚመኩበትን ምንም ነገር ሳይተውላቸው፣ እርሱም ለእነርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብ፣ ጽድቅ፣ ቅድሳትና ቤዛነት እንደተደረገላቸው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6