ትንቢተ ሶፎንያስ 3

AMHNIVአማርኛ20 ጥቅሶች4:24 አዳምጥ
አዳምጥ 4:24 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ለዐመፀኛዪቱና ለረከሰች፣ ለጨቋኞች ከተማ ወዮላት!

2እርሷ ለማንም አትታዘዝም፤ የማንንም ዕርምት አትቀበልም፤ በእግዚአብሔር አትታመንም፤ ወደ አምላኳም አትቀርብም።

3ሹሞቿ የሚያገሡ አንበሶች፣ ገዦቿ ለነገ የማይሉ፣ የምሽት ተኵላዎች ናቸው።

4ነቢያቷ ትዕቢተኞች፣ አታላዮችም ናቸው፤ ካህናቷ መቅደሱን ያረክሳሉ፣ በሕግም ላይ ያምፃሉ።

5በእርሷ ውስጥ ያለው እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፤ ፈጽሞ አይሳሳትም፤ በየማለዳው ቅን ፍርድ ይሰጣል፤ በየቀኑም አይደክምም፤ ዐመፀኞች ግን ዕፍረት አያውቁም።

6“ሕዝቦችን አጥፍቻለሁ፤ ምሽጋቸው ተደምስሶአል፤ ማንም እንዳያልፍባቸው፣ መንገዳቸውን ባድማ አደረግሁ፤ ከተሞቻቸው ተደምስሰዋል፤ አንድም ሰው የለም፤ ነዋሪም ከቶ አይገኝባቸውም።

7እኔም ከተማዪቱን፣ ‘በእርግጥ ትፈሪኛለሽ፤ ዕርምትም ትቀበያለሽ’ አልኋት፤ ስለዚህ መኖሪያዋ አይጠፋም፤ ቅጣቴም ሁሉ በእርሷ ላይ አይደርስም። እነርሱ ግን በሚያደርጉት ሁሉ፣ ክፋትንም በመፈጸም እየተጉ ሄዱ።

8እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለዚህ እስከምፈርድበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፤ አሕዛብን ላከማች፣ መንግሥታትን ልሰበስብ፣ መዓቴንና ጽኑ ቊጣዬን፣ በላያቸው ላፈስ ወስኛለሁ፤ በቅናቴ ቍጣ እሳት፣ መላዋ ምድር ትቃጠላለችና።

9“በዚያ ጊዜ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም እንዲጠሩ፣ ተስማምተው እንዲያገለግሉት፣ አንደበታቸውን አጠራለሁ።

10ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ፣ የሚያመልኩኝ፣ የተበተኑት ሕዝቤ ቊርባን ያመጡልኛል።

11በእኔ ላይ ከፈጸማችሁት በደል ሁሉ የተነሣ፣ በዚያ ቀን አታፍሩም፤ በትዕቢታቸው የሚደሰቱትን፣ ከዚህች ከተማ አስወግዳለሁና፤ ከእንግዲህ ወዲያ፣ በቅዱስ ተራራዬ ላይ አትታበዩብኝም።

12በእግዚአብሔር ስም የሚታመኑትን፣ የዋሃንንና ትሑታንን፣ በመካከላችሁ አስቀራለሁ።

13የእስራኤል ትሩፋን ኀጢአት አይሠሩም፤ ሐሰትም አይናገሩም፤ በአንደበታቸውም ተንኰል አይገኝም። ይበላሉ፤ ይተኛሉ፤ የሚያስፈራቸውም የለም።

14የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፤ እልል በይ፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፤ በፍጹም ልብሽ ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ።

15እግዚአብሔር ቅጣትሽን አስወግዶታል፤ ጠላቶችሽን ከአንቺ መልሶአል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው፤ ከእንግዲህ ወዲያ አንዳች ክፉ ነገር አትፈሪም።

16በዚያ ቀን ኢየሩሳሌምን እንዲህ ይሏታል፤ “ጽዮን ሆይ፤ አትፍሪ፤ እጆችሽም አይዛሉ።

17እግዚአብሔር አምላክሽ በመካከልሽ አለ፤ እርሱ ብርቱ ታዳጊ ነው፤ በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤ በዝማሬም በአንቺ ላይ ከብሮ ደስ ይሰኛል።”

18“ስለ ክብረ በዓላት መተጓጐል የተከዝሽበትን፣ የስድብሽን ሸክም፤ ከአንቺ አስወግዳለሁ።

19በዚያ ጊዜ፣ ያስጨነቁሽን ሁሉ እቀጣለሁ፤ አንካሶችን እታደጋለሁ፤ የተበተኑትንም እሰበስባለሁ፤ በተዋረዱበት ምድር ሁሉ፣ ለውዳሴና ለክብር አደርጋቸዋለሁ።

20በዚያን ጊዜ እሰበስባችኋለሁ፤ ያን ጊዜ ወደ አገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ ዐይናችሁ እያየ፣ ምርኮአችሁን በምመልስበት ጊዜ፣ መከበርንና መወደስን፣ በምድር ሕዝብ ሁሉ መካከል እሰጣችኋለሁ”፤ ይላል እግዚአብሔር።

ማብራሪያ

3:1-7 ቅዱሱ አምላክ ኃጢአትን በእርሱ ዘንድ ይበልጥ ቅርብ በሆኑት ላይ ከሁሉ በላይ ይጠላል። ኃጢአተኛነት አሁንና ወደፊትም የሰቆቃ ሁኔታ ነው። ሆኖም የእግዚአብሔር መገኘት ምልክቶች፣ ፈቃዱን የማወቅም የተሟሉ ጥቅሞች፣ እንዲሁም እርሱን እንዲያደርጉት እጅግ በርትተው የሚገፉ ምክንያቶች እያሏቸው፤ አሁንም በአለመታዘዝ ጸንተዋል። የሚያሳዝነው ግን፣ ሰዎች መልካምን ከሚያደርጉ አማኞች ይልቅ ክፉን በመሥራት ብዙ ጊዜ ይበልጥ ቅንዓተኛ ናቸው።

3:8-13 የወንጌል ስብከት ትንቢት ተነግሮለት ነበር፣ በአይሁድ ሕዝብ ላይም በቀል በሚፈጸምበት ጊዜ። የወንጌል የማንጻት ትምህርቶች፣ ወይም የጌታ የጸጋው ንጹሕ ቋንቋ፣ ሰዎችን የትሕትናን፣ የንስሓንና የእምነትን ቋንቋ እንዲናገሩ ያስተምር ነበር። በዕለት ተዕለት ንግግር ንጽሕናና እግዚአብሔርን መምሰል መልካም ነው። በመጨረሻው ዘመን የቤተ ክርስቲያን ንጹሕና ደስተኛ ሁኔታ የታሰበበት ይመስላል። ጌታ ትምክህትን ያጠፋል፤ ሰዎችንም ከጌታ ከኢየሱስ በቀር የሚመኩበትን ምንም ነገር ሳይተውላቸው፣ እርሱም ለእነርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብ፣ ጽድቅ፣ ቅድሳትና ቤዛነት እንደተደረገላቸው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6