ትንቢተ ሶፎንያስ 2

AMHNIVአማርኛ15 ጥቅሶች3:15 አዳምጥ
አዳምጥ 3:15 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እናንት ዕረፍት የሌላችሁ ሕዝብ ሆይ፤ በአንድነት ተሰብሰቡ፤ ተከማቹም፤

2የተወሰነው ጊዜ ሳይደርስ፣ ቀኑ እንደ ገለባ ሳይጠራርጋችሁ፣ የእግዚአብሔር ጽኑ ቊጣ በእናንተ ላይ ሳይመጣ፣ የእግዚአብሔር የመዓት ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ።

3እናንት የምድር ትሑታን ሁሉ፣ ትእዛዙን የምትፈጽሙ፣ እግዚአብሔርን እሹ፤ ጽድቅንና ትሕትናን ፈልጉ፤ በእግዚአብሔር የቊጣ ቀን፣ ትሰወሩ ይሆናል።

4ጋዛ ባድማ ትሆናለች፤ አስቀሎናም ፈራርሳ ትቀራለች፤ አዛጦን በቀትር ባዶ ትሆናለች፤ አቃሮንም ትነቀላለች።

5እናንት በባሕር ዳርቻ የምትኖሩ፣ የከሊታውያን ሰዎች ሆይ፤ ወዮላችሁ የፍልስጥኤማውያን ምድር ከነዓን ሆይ፤ በአንቺ ላይ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ “ፍጹም አጠፋሻለሁ፤ ከነዋሪዎችሽም የሚተርፍ የለም።”

6የቀርጤስ ሰዎች የሚኖሩበት በባሕሩ ዳር ያለው ምድር፣ የእረኞች መኖሪያና የበጎች በረት ይሆናል፤

7ይህም ለይሁዳ ቤት ትሩፍ ይሰጣል፤ እነርሱም በዚያ መሰማሪያ ያገኛሉ። በአስቀሎና ቤቶች ውስጥም፣ በምሽት ይተኛሉ፤ አምላካቸው እግዚአብሔር ይጠብቃቸዋል፤ ምርኮአቸውንም ይመልስላቸዋል።

8“የሞዓብን ስድብ፣ የአሞናውያንንም ፌዝ ሰምቻለሁ፤ ሕዝቤን ሰድበዋል፤ በምድራቸውም ላይ ዝተዋል።

9ስለዚህ የእስራኤል አምላክ፣ ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሕያውነቴ እምላለሁ ሞዓብ እንደ ሰዶም፣ አሞናውያን እንደ ገሞራ፣ ዐረም እንደ ዋጠው ቦታና እንደ ጨው ጒድጓድ ለዘላለም ጠፍ ይሆናሉ። ከሕዝቤ የቀሩት ይዘርፏቸዋል፤ ከወገኔ የተረፉትም ምድራቸውን ይወርሳሉ።”

10ከትዕቢታቸው የተነሣ የሚደርስባቸው ይህ ነው፤ የሁሉን ገዥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሰድበው ዘብተውበታልና፣

11እግዚአብሔር የምድሪቱን አማልክት ሁሉ በሚደመስስበት ጊዜ፣ በእነርሱ ዘንድ የተፈራ ይሆናል፤ በየባሕሩ ጠረፍ የሚኖሩ ሕዝቦች፣ እያንዳንዳቸው በያሉበት ሆነው ለእርሱ ይሰግዳሉ።

12“ኢትዮጵያውያን ሆይ፤ እናንተም፣ በሰይፌ ትገደላላችሁ።”

13እጁን በሰሜን ላይ ይዘረጋል፤ አሦርንም ያጠፋል፤ ነነዌን ፍጹም ባድማ፣ እንደ ምድረ በዳም ደረቅ ያደርጋታል።

14የበግና የከብት መንጋዎች፣ የፍጥረት ዐይነት ሁሉ በውስጧ ይመሰጋሉ፤ ጒጒትና ጃርት፣ በግንቦቿ ላይ ያድራሉ። ጩኸታቸው በየመስኮቱ ያስተጋባል፤ ፍርስራሽ በየደጃፉ ይከመራል፤ ከዝግባ የተሠሩ ተሸካሚዎችም ይገለጣሉ።

15ተዘልላ የኖረች፣ ደስተኛዪቱ ከተማ ይህች ናት፤ እርሷም በልቧ፣ “እኔ ብቻ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ማንም የለም” ያለች፣ ታዲያ እንዴት የዱር አራዊት የሚመሰጉባት፣ ባድማ ሆና ቀረች? በአጠገቧ የሚያልፉ ሁሉ፣ ያፌዙባታል፤ እጃቸውንም በንቀት ያወዛውዙባታል።

ማብራሪያ

2:1-3 ነቢዩ፣ ሀገራዊ ጥፋትን ለመከላከል ብቸኛው መንገድ እንደመሆኑ መጠን፣ ለሀገራዊ ንስሐ ጥሪ ያደርጋል። እግዚአብሔርን የማትሻ፣ ወደ እግዚአብሔርም ምኞት የሌላት ሀገር፣ የእርሱን ሞገስና ጸጋ አትፈልግም፤ ንስሐ ለመግባትና ለመታደስም ፍላጎት የላትም። ወይም ደግሞ፣ ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርባት የሚችል ምንም ነገር የሌላትና እግዚአብሔር ዘንድ የማትወደድ ሀገር ናት፤ እግዚአብሔርም በትክክል “ከእኔ ራቁ” ሊላት ይችል የነበረ ቢሆንም፣ እርሱ ግን “ፊቴን ትሹ ዘንድ ወደ እኔ ተሰብሰቡ” ይላል። የእግዚአብሔር ድንጋጌ በማይጸጸቱ ኃጢአተኞች ላይ ምን እንደሚያመጣ እናውቃለን፤ ስለዚህም ሁሉም ሰው በጸጋው ዘመን ንስሐ እንዲገባ በጥልቀት ሊያሳስበው ይገባል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6