1ነፍሴ ዕረፍት የምታገኘው በእግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ድነቴም የሚመጣልኝ ከእርሱ ዘንድ ነው።
2ዐለቴና መድኀኒቴ እርሱ ብቻ ነው፤ መጠጊያዬም እርሱ ነው፤ ከቶም አልናወጥም።
3ሰውን የምታጠቁት እስከ መቼ ነው? ይህን የዘመመ ግድግዳ፣ የተንጋደደ ዐጥር፣ ሁላችሁ ገፍታችሁ ልትጥሉት ትሻላችሁ?
4ከታላቅ ክብሩ ሊያዋርዱት፣ ይህን አንድ ነገር ወጠኑ፤ ሐሰት ባለበት ነገር ደስ ይሰኛሉ፤ በአፋቸው ይመርቃሉ፤ በልባቸው ግን ይራገማሉ። ሴላ
5ነፍሴ ሆይ፤ ዐርፈሽ እግዚአብሔርን ብቻ ጠብቂ፤ ተስፋዬ ከእርሱ ዘንድ ነውና።
6ዐለቴና መድኀኒቴ እርሱ ብቻ ነው፤ መጠጊያዬም እርሱ ነው፤ እኔም አልናወጥም።
7መዳኔና ክብሬ በእግዚአብሔር ነው፤ ብርቱ ዐለቴና መሸሸጊያዬ በእግዚአብሔር ነው።
8ሰዎች ሆይ፤ ሁል ጊዜ በእርሱ ታመኑ፤ ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ፤ እግዚአብሔር መጠጊያችን ነውና። ሴላ
9ከተናቀ ወገን መወለድ ከንቱ፣ ከከበረውም መወለዱ ሐሰት ነው። በሚዛን ላይ ከፍ ብለው ቢታዩም፣ ሁሉም በአንድነት ከነፋስ የቀለሉ ናቸው።
10በዝርፊያ አትታመኑ፤ በቅሚያም ተስፋ አታድርጉ፤ በዚህ ብትበለጽጉም፣ ልባችሁ ይህን አለኝታ አያድርግ።
11እግዚአብሔር አንድ ነገር ተናገረ፤ እኔም ይህን ሁለት ጊዜ ሰማሁ፤ ኀይል የእግዚአብሔር ነው።
12ጌታ ሆይ፤ ምሕረትም የአንተ ነው፤ አንተ ለእያንዳንዱ፣ እንደ ሥራው ትከፍለዋለህ።