1ምድርና በእርሷ ያለው ሁሉ፣ ዓለምና በውስጧ የሚኖር ሁሉ የእግዚአብሔር ነው፤
2እርሱ በባሕሮች ላይ መሥርቶአታልና፤ በውሆችም ላይ አጽንቶአታል።
3ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ሊወጣ ይችላል? በተቀደሰ ስፍራውስ ማን ይቆማል?
4ንጹሕ እጅና ቅን ልብ ያለው፤ ነፍሱን ለሐሰት ነገር የማያስገዛ፤ በውሸት የማይምል፤
5እርሱ በረከትን ከእግዚአብሔር ዘንድ፣ ምሕረትንም ከአዳኝ አምላኩ ይቀበላል።
6እርሱን የሚፈልግ ትውልድ እንዲህ ነው፤ የያዕቆብ አምላክ ሆይ፤ ፊትህን የሚፈልግ እንዲህ ያለ ነው። ሴላ
7እናንተ ደጆች፤ ቀና በሉ፤ እናንተ የዘላለም በሮች፤ የክብር ንጉሥ እንዲገባ ብድግ በሉ!
8ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? እግዚአብሔር ነው ብርቱና ኀያል፤ እግዚአብሔር ነው በውጊያ ኀያል።
9እናንተ ደጆች፤ ቀና በሉ፤ እናንተ የዘላለም በሮች፤ የክብር ንጉሥ እንዲገባ ብድግ በሉ!
10ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? የሰራዊት አምላክ፣ እርሱ የክብር ንጉሥ ነው። ሴላ