የማርቆስ ወንጌል 11

AMHNIVአማርኛ33 ጥቅሶች5:18 አዳምጥ
አዳምጥ 5:18 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ወደ ኢየሩሳሌም በደብረ ዘይት ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ በማለት ላካቸው፤

2“በፊታችሁ ወዳለው መንደር ሂዱ፣ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ የአህያ ውርንጫ እዚያ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈታችሁ አምጡት፤

3ማንም፣ ‘ምን ማድረጋችሁ ነው?’ ቢላችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል፤ በቶሎም መልሶ ይልከዋል’ ብላችሁ ንገሩት።”

4እነርሱም ሄዱ፤ በአንድ ቤት በራፍ እመንገድ ላይ የአህያ ውርንጫ ታስሮ አገኙት፤ ፈቱትም።

5በዚያ ከቆሙት አንዳንድ ሰዎች፣ “ውርንጫውን የምትፈቱት ለምንድን ነው?” አሏቸው።

6ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ያላቸውን ለሰዎቹ በነገሯቸው ጊዜ ፈቀዱላቸው።

7ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አምጥተው ልብሳቸውን በጀርባው ላይ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠበት።

8ብዙ ሰዎች ልበሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ ለምለም የዛፍ ቅርንጫፍ እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር።

9ከፊቱ የቀደሙትና ከኋላው የተከተሉትም በታላቅ ድምፅ፤ እንዲህ ይሉ ነበር፤ “ሆሣዕና! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!

10የምትመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት! ሆሣዕና በአርያም!”።

11ኢየሱስም ኢየሩሳሌም ደረሰ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ ተመለከተ፤ ቀኑም ስለመሸ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ።

12በማግሥቱ ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ።

13እርሱም ቅጠል ያላት የበለስ ዛፍ ከሩቅ አየ፤ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደሆነ ብሎ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም።

14ከዚያም ዛፏን፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ፍሬ ከአንቺ አይብላ” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙ።

15ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤

16ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ።

17ሲያስተምራቸውም፣ “ ‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት!” አላቸው።

18የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም፣ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና።

19በመሸም ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ።

20በማግስቱ ጠዋት በመንገድ ሲያልፉ፣ በለሲቱ ከነሥሯ ደርቃ አዩ።

21ጴጥሮስ ነገሩ ትዝ አለውና ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ እነሆ፤ የረገምሃት በለስ ደርቃለች” አለው።

22ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “በእግዚአብሔር እመኑ፤

23እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ይህን ተራራ፣ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ቢለውና ይህንንም በልቡ ሳይጠራጠር ቢያምን ይሆንለታል።

24ስለዚህ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ እንደ ተቀበላችሁት አድርጋችሁ ብታምኑ ይሆንላችኋል።

25እንዲሁም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ፣ የሰማዩ አባታችሁ ኀጢአታችሁን ይቅር እንዲልላችሁ፣ እናንተም በሰው ላይ ያላችሁን ሁሉ ይቅር በሉ።

26ይቅር ባትሉ ግን የሰማዩ አባታችሁ ኀጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።”

27እንደ ገና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚዘዋወርበት ጊዜ፣ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ቀርበው፣

28“እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? እነዚህን እንድታደርግስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው” አሉት።

29ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እስቲ እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ መልሱልኝ፤ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ።

30የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ።”

31እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “ ‘ከሰማይ ነው’ ብንል፣ ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤

32‘ታዲያ፣ ከሰው ነው’ እንበልን?” ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ እውነተኛ ነቢይ መሆኑን ያምኑ ስለ ነበር ፈሩ።

33ስለዚህ ለኢየሱስ “አናውቅም” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም፣ “እንግዲያው እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።

ማብራሪያ

11:1-11 የክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም በዚህ ዓይነት አስደናቂ ሁኔታ መግባት የጠላቶቹን ኃይልና ክፋት እንዳልፈራ ያሳያል። ይህ በፍርሃት የተሞሉ የነበሩትን ደቀ መዛሙርቱን ያበረታታ ነበር። ደግሞም ስለሚመጡት መከራዎቹ በማሰብ እንዳልተረበሸ ያሳያል። ነገር ግን ይህ ሁሉ ትሕትናውን ያሳያል፤ እነዚህም ነገሮች ከፍ ከፍ ያሉትን ነገሮች እንዳንሻ፣ ነገር ግን ራስን ዝቅ አድርገን ከትሑታን ጋር እንድንሆን ያስተምሩናል። ክርስቶስ ይህን የራሱ ነው ከማለት የራቀ በነበረ ጊዜ፣ ክርስቲያኖች እንደዚህ ራሳቸውን ከፍ ከፍ ማድረጋቸው እንዴት አስቀያሚ ነው! ሰውንነቱን በደስታ ተቀበሉት፤ እርሱም፡- “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!” ተብሎ የተነገረለት፣ በተደጋጋሚ ተስፋ የተሰጠለትና ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲጠበቅ የነበረው እርሱ ነው። ምርጥ ፍቅራችንን ለእርሱ እንስጥ፤ እርሱ የተባረከ አዳኝ ነውና፣ በረከትንም ለእኛ ያመጣልናል፣ እርሱን የላከውም የተባረከ ይሁን። በሰማያት ከሁሉ በላይ ከፍ ብሎ ለሚኖረው፣ ከሁሉ በላይ ለሆነው፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም የተባረከ ለሆነው አምላካችን ምስጋና ይሁን።

11:12-18

ክርስቶስ ፍሬን ሊያገኝ ተመለከተ፤ የበለስን የመሰብሰብ ጊዜው ቅርብ ቢሆንም ገና አልደረሰም ነበር፤ ነገር ግን አላገኘም። እርሱ ይህችን በለስ ለዛፎች ሳይሆን ለዚያ ትውልድ ሰዎች ምሳሌ አደረጋት።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6