ትንቢተ ሚክያስ 3

AMHNIVአማርኛ12 ጥቅሶች2:24 አዳምጥ
አዳምጥ 2:24 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ከዚያም እኔ እንዲህ አልሁ፤ “እናንት የያዕቆብ መሪዎች፤ እናንት የእስራኤል ቤት ገዦች ስሙ፤ ፍትሕን ማወቅ አይገባችሁምን?

2መልካሙን ጠላችሁ፤ ክፉውንም ወደዳችሁ፤ የሕዝቤን ቈዳ ገፈፋችሁ፤ ሥጋቸውንም ከዐጥንቶቻቸው ለያችሁ፤

3የሕዝቤን ሥጋ በላችሁ፤ ቈዳቸውን ገፈፋችሁ፤ ዐጥንቶቻቸውንም ሰባበራችሁ፤ በመጥበሻ እንደሚጠበስ፣ በድስት እንደሚቀቀል ሥጋ ቈራረጣችኋቸው።

4እነርሱም ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፤ እርሱ ግን አይመልስላቸውም፤ ካደረጉት ክፋት የተነሣ፣ በዚያ ጊዜ ፊቱን ከእነርሱ ይሰውራል።

5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቤን የሚያስቱ ነቢያት፣ ሰው ሲያበላቸው፣ ‘ሰላም አለ’ ይላሉ፤ ሳያበላቸው ሲቀር ግን፣ ጦርነት ሊያውጁበት ይነሣሉ።

6ስለዚህ ሌሊቱ ያለ ራእይ፣ ጨለማውም ያለ ንግርት ይመጣባችኋል፤ በነቢያት ላይ ፀሐይ ትጠልቅባቸዋለች፤ ቀኑም ይጨልምባቸዋል።

7ባለራእዮች ያፍራሉ፤ ንግርተኞችም ይዋረዳሉ፤ ሁሉም ፊታቸውን ይሸፍናሉ፤ ከእግዚአብሔር መልስ የለምና።”

8እኔ ግን፣ ለያዕቆብ በደሉን፣ ለእስራኤልም ኀጢአቱን እነግር ዘንድ ኀይልን፣ በእግዚአብሔር መንፈስ፣ ፍትሕና ብርታት ተሞልቻለሁ።

9እናንት የያዕቆብ ቤት መሪዎች፣ እናንት የእስራኤል ቤት ገዦች፣ ፍትሕን የምትንቁ፤ ትክክለኛ የሆነውንም ነገር ሁሉ የምታጣምሙ፤ ስሙ፤

10ጽዮንን ደም በማፍሰስ፣ ኢየሩሳሌምን በክፋት የምትገነቡ፤ ስሙ።

11መሪዎቿ በጒቦ ይፈርዳሉ፤ ካህናቷ ለዋጋ ሲሉ ያስተምራሉ፤ ነቢያቷም ለገንዘብ ሲሉ ይናገራሉ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ተደግፈውም፣ “እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ምንም ዐይነት ክፉ ነገር አይደርስብንም” ይላሉ።

12ስለዚህ በእናንተ ምክንያት፣ ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፣ ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች፤ የቤተ መቅደሱም ኰረብታ ዐረም የበቀለበት ጒብታ ይሆናል።

ማብራሪያ

3:1-8 ሰዎች ክፉ ነገር እያደረጉ መልካም ሊሆንላቸው አይጠብቁም፤ ይልቁንም ለሌሎች ያደረጉትን በእነርሱ ላይ ሲደረግ ያገኛሉ። ጠቃሚ እውነቶች በከፍተኛ ስፍራ ወይም በሥልጣን ላይ ባሉ ሰዎች ጆሮ የሚደርሱት ምን ያህል አልፎ አልፎ ነው! ሌሎችን የሚያታልሉ ሰዎች ለራሳቸው ፊት ውርደትን ያዘጋጃሉ። ነቢዩ ለእግዚአብሔርና ለሰዎች ነፍሳት ጥልቅ ፍቅር ነበረው፤ ለክብሩና ለድነታቸው ጥልቅ ስጋት፣ እንዲሁም በኃጢአት ላይ ቅንዓት ነበረው። ያጋጠሙት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከሥራው አላስቆሙትም። ይህ ጥንካሬ የነበረው ከራሱ ወይም በራሱ አልነበረም፤ ነገር ግን በጌታ መንፈስ በኃይል የተሞላ ነበር።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6