1በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ወደ ሞሬታዊው ወደ ሚክያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል፣ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ ይህ ነው፤
2እናንተ አሕዛብ ሆይ፤ ሁላችሁም ስሙ፤ ምድር ሆይ፤ በውስጧም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ፤ ጌታ ከቅዱስ መቅደሱ፣ ልዑል እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ይመሰክርባችኋል።
3እነሆ፤ እግዚአብሔር ከመኖሪያ ስፍራው ይመጣል፤ ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይራመዳል።
4ተራሮች ከሥሩ ይቀልጣሉ፤ ሸለቆዎችም ይሰነጠቃሉ፤ በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፣ በገደል ላይ እንደሚወርድ ፈሳሽ ይሆናሉ።
5ይህ ሁሉ የሚሆነው ስለ ያዕቆብ በደል፣ ስለ እስራኤልም ቤት ኀጢአት ነው። የያዕቆብ በደል ምንድን ነው? ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ የኰረብታ መስገጃ ምንድን ነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን?
6“ስለዚህ ሰማርያን የፍርስራሽ ክምር፣ ወይን የሚተከልባትም ስፍራ አደርጋታለሁ፤ ድንጋዮቿን ወደ ሸለቆ አወርዳለሁ፤ መሠረቷንም ባዶ አደርጋለሁ።
7ጣዖቶችዋ ሁሉ ይሰባበራሉ፤ ለቤተ መቅደሷ የቀረበው ገጸ በረከት በእሳት ይቃጠላል፤ ምስሎችዋን ሁሉ እደመስሳለሁ፤ ገጸ በረከቷን በዝሙት አዳሪነት እንደ ሰበሰበች ሁሉ፣ አሁንም ገጸ በረከትዋ የዝሙት አዳሪነት ዋጋ መቀበያ ይሆናል።
8በዚህ ምክንያት አለቅሳለሁ፤ ዋይ ዋይም እላለሁ፤ ባዶ እግሬንና ዕርቃኔን እሄዳለሁ፤ እንደ ቀበሮ አላዝናለሁ፤ እንደ ጒጒትም አቃስታለሁ።
9ቊስሏ የማይሽር ነውና፤ ለይሁዳ ተርፎአል፤ እስከ ሕዝቤ መግቢያ በር፣ እስከ ኢየሩሳሌም እንኳ ደርሶአል።
10በጌት አታውሩት፤ ከቶም አታልቅሱ፤ በቤትዓፍራ፣ በትቢያ ላይ ተንከባለሉ።
11እናንት በሻፊር የምትኖሩ፣ ዕርቃናችሁን ሆናችሁ በኀፍረት ዕለፉ፤ በጸዓናን የሚኖሩ ከዚያ አይወጡም፤ ቤትዔጼል በሐዘን ላይ ናት፤ ለእናንተም መጠጊያ ልትሆን አትችልም።
12ከመከራው መገላገልን በመሻት፣ በማሮት የሚኖሩ በሥቃይ ይወራጫሉ፤ እስከ ኢየሩሳሌም በር ሳይቀር፣ ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቶአልና።
13እናንት በለኪሶ የምትኖሩ፣ ፈረሶችን ከሠረገላው ጋር አያይዙ፤ ለጽዮን ሴት ልጅ፣ የኀጢአት መጀመሪያ እናንት ነበራችሁ፤ የእስራኤል በደል በእናንተ ዘንድ ተገኝቶአልና።
14ስለዚህ እናንተ ለሞሬሼትጌት፣ ማጫ ትሰጣላችሁ፤ የአክዚብ ከተማ፣ ለእስራኤል ነገሥታት መታለያ ትሆናለች።
15እናንት በመሪሳ የምትኖሩ ድል አድራጊ አመጣባችኋለሁ፤ ያ የእስራኤል ክብር የሆነው ወደ ዓዶላም ይመጣል።
16ደስ ለምትሰኙባቸው ልጆቻችሁ፣ በሐዘን ራሳችሁን ተላጩ፤ ራሳችሁን እንደ አሞራ ራስ ተመለጡት፤ ከእናንተ በምርኮ ይወሰዳሉና።