1በሰንበትም መጨረሻ መጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ።
2እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ።
3መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ።
4ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ሆኑ።
5መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው፦ “እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤
6እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ።
7ፈጥናችሁም ሂዱና፦ ‘ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ፥’ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። እነሆም፥ ነገርኋችሁ።”
8በፍርሃትና በታላቅ ደስታም ፈጥነው ከመቃብር ሄዱ፥ ለደቀ መዛሙርቱም ሊያወሩ ሮጡ።
9እነሆም፥ ኢየሱስ አገኛቸውና፦ “ደስ ይበላችሁ፡” አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት።
10በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፤ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ፥ በዚያም ያዩኛል።”
11ሲሄዱም ሳሉ እነሆ፥ ከጠባቆቹ አንዳንድ ወደ ከተማ መጥተው የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩ።
12ከሽማግሎች ጋርም ተሰብስበው ተማከሩና ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥተዋቸው፦
13“እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት፡” በሉ።
14ይህም በገዢው ዘንድ የተሰማ እንደ ሆነ፥ እኛ እናስረዳዋለን እናንተም ያለ ሥጋት እንድትሆኑ እናደርጋለን አሉአቸው።
15እነርሱም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ አስተማሩአቸው አደረጉ። ይህም ነገር በአይሁድ ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ሲወራ ይኖራል።
16አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፥
17ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ የተጠራጠሩ ግን ነበሩ።
18ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ።
19“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”