1ሰንበት ካለፈ በኋላ፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ጎሕ ሲቀድ፣ ማርያም መግደላዊትና ሌላዋ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ ሄዱ።
2በድንገት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የጌታም መልአክ ከሰማይ ወርዶ ወደ መቃብሩ በመሄድ ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ላይ ተቀመጠበት፤
3መልኩ እንደ መብረቅ ብሩህ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበር።
4ጠባቂዎቹ መልአኩን ከመፍራት የተነሣ ተንቀጠቀጡ፤ እንደ በድንም ሆኑ።
5መልአኩም ሴቶቹን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ አውቃለሁና፤
6እርሱ በዚህ የለም፤ እንደ ተናገረው ተነሥቶአል፤ ኑና ተኝቶበት የነበረውን ቦታ እዩ።
7አሁንም ፈጥናችሁ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱ፣ ‘ከሙታን ተነሥቶአል፤ ቀድሞአችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ በዚያ ታዩታላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው። እንግዲህ ነግሬአችኋለሁ!”
8ሴቶቹም በፍርሀትና በደስታ ተሞልተው ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር በፍጥነት እየሮጡ የመቃብሩን ስፍራ ትተው ሄዱ።
9ወዲያው ኢየሱስ አገኛቸውና፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት።
10ኢየሱስም፣ “አትፍሩ፤ ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ በዚያ ያዩኛል” አላቸው።
11ሴቶቹ በመንገድ ላይ ሳሉ፣ ከጠባቂዎቹ ጥቂቶቹ ወደ ከተማ በመሄድ የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩላቸው።
12የካህናት አለቆችም ከሽማግሌዎች ጋር ተሰብስበው ተማከሩ፤ ለወታደሮቹ በቂ ገንዘብ በመስጠት
13እንዲህ አሏቸው፤ “ ‘ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት’ በሉ፤
14ይህ ወሬ በገዥው ዘንድ ቢሰማ እንኳ፣ እኛ እናስረዳዋለን፤ ምንም ክፉ ነገር እንዳይደርስባችሁ እናደርጋለን።”
15ወታደሮቹም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ ታዘዙት አደረጉ። ይህም ታሪክ እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁዶች ዘንድ በሰፊው እንደተሰራጨ ነው።
16ከዚያም ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት በገሊላ ወዳለው ኢየሱስ ወዳመለከታቸው ተራራ ሄዱ።
17ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ ጥቂቶች ግን ተጠራጠሩ።
18ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት ቀርቦ እንዲህ አላቸው፤ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤
19ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤
20ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”