የሉቃስ ወንጌል 2

AMHNIVአማርኛ52 ጥቅሶች7:35 አዳምጥ
አዳምጥ 7:35 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በዚያን ዘመን፣ የዓለሙ ሁሉ ሕዝብ እንዲቈጠርና እንዲመዘገብ ከአውግስጦስ ቄሳር ትእዛዝ ወጣ።

2ይህም ቄሬኔዎስ የሶርያ ገዢ በነበረበት ጊዜ የተደረገ የመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ ነበር።

3ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ለመመዝገብ ወደየራሱ ከተማ ሄደ።

4ዮሴፍም ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ፣ በገሊላ አውራጃ ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ የዳዊት ከተማ ወደሆነችው፣ ቤተ ልሔም ወደምትባል ከተማ ወደ ይሁዳ ወጣ።

5ወደዚያም ለመመዝገብ የተጓዘው፣ የመውለጃ ጊዜዋ ከተቃረበው ከእጮኛው ከማርያም ጋር ነበር።

6በዚያም እንዳሉ የምትወልድበት ጊዜ ደረሰ፤

7የበኵር ልጇ የሆነውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ በጨርቅም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማረፊያ ቦታ ስላላገኙ በግርግም አስተኛችው።

8በዚያው አገር በሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ በሜዳ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ።

9የጌታም መልአክ ድንገት መጥቶ በአጠገባቸው ቆመ፤ የጌታም ክብር በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅም ፍርሀት ያዛቸው።

10መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች አምጥቼላችኋለሁና።

11ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀን ተወልዶላችኋልና፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው።

12ይህ ምልክት ይሁናችሁ፤ ሕፃን ልጅ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ።”

13ድንገትም ብዙ የሰማይ ሰራዊት ከመልአኩ ጋር ታዩ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ እንዲህ አሉ፤

14“ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱ ለሚወዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!”

15መላእክቱ ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ ከወጡ በኋላ እረኞቹ፣ “ጌታ የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንድናይ ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ” ተባባሉ።

16እነርሱም ፈጥነው ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን፣ ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ።

17ካዩም በኋላ፣ ስለ ሕፃኑ የተነገራቸውን ገልጠው አወሩ።

18ይህንንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ፤

19ማርያም ግን ይህንን ሁሉ በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር።

20እረኞቹም ሁሉም ነገር እንደ ተነገራቸው ሆኖ በማግኘታቸው፣ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ።

21ስምንት ቀን ሆኖት የመገረዣ ጊዜው ሲደርስ፣ ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስም ኢየሱስ ተባለ።

22በሙሴ ሕግ መሠረት፣ የመንጻታቸው ወቅት በተፈፀመ ጊዜ፣ ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ለጌታ ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ወጡ፤

23ይኸውም በጌታ ሕግ፣ “ተባዕት የሆነ በኵር ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል” ተብሎ እንደ ተጻፈ ለመፈጸምና

24ደግሞም በጌታ ሕግ፣ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፣” መሥዋዕት ለማቅረብ ነበር።

25በዚያን ጊዜ ጻድቅና ትጒሕ የሆነ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው በኢየሩሳሌም ይኖር ነበር፤ እርሱም የእስራኤልን መጽናናት የሚጠባበቅና መንፈስ ቅዱስ በላዩ ያደረሰው ነበር።

26ደግሞም የጌታን መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ነበር፤

27እርሱም በዚህ ጊዜ በመንፈስ ተመርቶ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ የልጁም ወላጆች በሕጉ ልማድ መሠረት ተገቢውን ሊፈጽሙለት ሕፃኑን ኢየሱስን ይዘው በገቡ ጊዜ፣

28ስምዖን ተቀብሎ ዐቀፈው፤ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንዲህ አለ፤

29“ጌታ ሆይ፤ ቃል በገባኸው መሠረት፣ አሁን ባሪያህን በሰላም አሰናብተው፤

30ዐይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን፣

31ማዳንህን አይተዋልና።

32ይህም ለአሕዛብ መገለጥን የሚሰጥ ብርሃን፣ ለሕዝብህ ለእስራኤልም ክብር ነው።”

33አባቱና እናቱም ስለ እርሱ በተነገረው ነገር ተገረሙ።

34ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፤ “ይህ ሕፃን በእስራኤል ለብዙዎች መነሣትና መውደቅ ምክንያት እንዲሆን፣ ደግሞም ክፉ ለሚያስወሩበት ምልክት እንዲሆን ተወስኖአል፤

35የብዙዎችም የልብ ሐሳብ የተገለጠ እንዲሆን፣ የአንቺም ነፍስ ደግሞ በሰይፍ ይወጋል።”

36ደግሞም ከአሴር ወገን የሆነች የፋኑኤል ልጅ፣ ሐና የምትባል ነቢይት በዚያ ነበረች፤ እርሷም በጣም አርጅታ ነበር፤ በድንግልናዋ ካገባችው ባሏም ጋር ሰባት ዓመት የኖረች ነበረች፤

37ዕድሜዋም ሰማንያ አራት ዓመት እስኪሆናት ድረስ ቀንና ሌሊት ከቤተ መቅደስ ሳትለይ፣ በጾምና በጸሎት የምታገለግል መበለት ሆና ቈየች።

38በዚያኑም ጊዜ ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም መቤዠት ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ ሕፃኑ ተናገረች።

39ዮሴፍና ማርያም በጌታ ሕግ የታዘዘውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ፣ በገሊላ አውራጃ ወዳለችው ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ።

40ሕፃኑም እያደገና እየጠነከረ ሄደ፤ በጥበብ ተሞላ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ።

41ወላጆቹም በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር።

42ልጁም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ፣ እንደተለመደው ወደ በዓሉ ወጡ።

43በዓሉን ከፈጸሙ በኋላ፣ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፣ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀረ፤ ወላጆቹ ግን መቅረቱን አላወቁም ነበር።

44አብሮአቸው ያለ መስሎአቸው፣ የአንድ ቀን መንገድ ተጓዙ፤ በኋላ ግን ከዘመዶቻቸውና ከወዳጆቻቸው ዘንድ ይፈልጉት ጀመር፤

45ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

46ከሦስት ቀንም በኋላ፣ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው በቤተ መቅደስ ውስጥ አገኙት፤

47የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይደነቁ ነበር።

48ወላጆቹም ባዩት ጊዜ ተገረሙ፤ እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለምን እንዲህ አደረግኸን? አባትህና እኔኮ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር” አለችው።

49እርሱም፣ “ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መገኘት እንደሚገባኝ አላወቃችሁምን?” አላቸው።

50እነርሱ ግን የተናገራቸው ነገር አልገባቸውም።

51ከዚያም አብሮአቸው ወደ ናዝሬት ወረደ፤ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር።

52ኢየሱስም በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ።

ማብራሪያ

ቊጥር ፪፥፩-፯ የዘመኑ ፍጻሜ አሁን ደርሶ ነበር፤ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ከሴት የተወለደ፣ ከሕግም በታች የሆነ አድርጎ ላከ። የትውልዱ ሁኔታዎች እጅግ በጣም ትሑት ነበሩ። ክርስቶስ የተወለደው በእንግዳ ማረፊያ ውስጥ ነበር፤ እርሱ ወደ ዓለም የመጣው እዚህ እንደ እንግዳ ማረፊያ ቤት ለጥቂት ጊዜ እንግዳ ሆኖ ለመኖርና እኛም እንደዚሁ እንድናደርግ ሊያስተምረን ነው። እኛ በኃጢአት ምክንያት ረዳት የሌለውና የተተወ እንደ ተጣለ ሕፃን ሆነናል፤ ክርስቶስም እንደዚህ ያለ ሆነ። እርሱ በትሑት ሁኔታ ለመኖር፣ ለመልበስ ወይም ለመመገብ ምን ያህል እንደማንሻ፤ ልጆቻችን እንዲያጌጡና እንዲንከባከቡ እንዴት እንደምንመኝ፤ ድሆች ሀብታሞችን ለመቅናት ምን ያህል እንደሚያዘነብሉ፤ ሀብታሞችም ድሆችን ለመናቅ ምን ያህል እንደሚያዘነብሉ በሚገባ ያውቅ ነበር። ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጅ ሰው ሲሆንና በግርግምም ሲተኛ እኛ በእምነት ስንመለከት፣ ከንቱነታችን፣ ከፍተኛ ምኞታችንና ቅናታችን ይታገድበታል። ይህንን ነገር በትክክል በፊታችን አድርገን፣ ለራሳችን ወይም ለልጆቻችን ታላላቅ ነገሮችን ልንሻ አንችልም።

2:8-20 መላእክት የአዲስ የተወለደው አዳኝ አዋጅ ነጋሪዎች ነበሩ፣ ነገር ግን የተላኩት ጥሪያቸውን እየፈጸሙ መንጎቻቸውን ይጠብቁ የነበሩ ድሆች፣ ትሑቶች፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩና ታታሪ እረኞች ዘንድ ብቻ ነበር። ቅን የሆነ ሥራ ስንሠራና በዚያም በእርሱ ጸንተን ስንኖር፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ከመጎብኘት አንርቅም። የዚህ ሥራ ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን፤ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን። መሲሑን በመላክ የተገለጠው የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ለሰው ልጆች ለእርሱ ውዳሴ ይሆናል። ሌሎች የእግዚአብሔር ሥራዎች ለክብሩ ናቸው፣ ነገር ግን የዓለም ቤዛነት ለክብሩ በአርያም ነው። መሲሑን በመላክ የተገለጠው የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ወደዚህ ታችኛው ዓለም ሰላምን አመጣ። እዚህ ላይ ሰላም የሚያመለክተው ክርስቶስ ሰብአዊ ተፈጥሮአችንን በመውሰዱ ከእርሱ ወደ እኛ የሚፈስሰውን መልካም ነገር ሁሉ ነው። ይህ የታመነ ቃል ነው፤ በማይቆጠሩ የመላእክት ሠራዊት የተረጋገጠ፣ በሙሉ ልብም መቀበል የሚገባው፣ የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ለሰው ልጆች በአርያም ለእግዚአብሔር ክብር፣ በምድርም ላይ ሰላም መሆኑ ነው። እረኞቹ ጊዜ አላባከኑም፣ ይልቁንም በችኮላ ወደ ስፍራው መጡ። እነርሱም ተረድተው ነበር፤ እርሱ አዳኝ፣ ጌታ ክርስቶስ እንደሆነም ስለዚህ ሕፃን በየአገሩ አውጅተዋል። ማርያምም እነዚህን ነገሮች ሁሉ በትኩረት ታስተውልና ታሰላስል ነበር፤ እነርሱም ቅዱስ ስሜቷን ለማነቃቃት እጅግ የተስማሙ ነበሩ። እነዚህን ነገሮች በልባችን ይበልጥ አብዝተን ብናሰላስል ኖሮ፣ በፍርድና በሥራ ከስህተቶች ይበልጥ እንድንድን ነበር። ለእኛ አዳኝ፣ ጌታ ክርስቶስ መወለዱ እስካሁንም በጆሮአችን ይታወጃል። ይህም ለሁሉ ታላቅ የምስራች መሆን አለበት።

2:21-24 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአት አልተወለደም ነበር፤ ስለሆነም በግርዘት የሚጠቁመውን የረከሰውን ባሕርይ የማጥፋት ወይም ደግሞ ወደ ቅድስና የመታደስ አያስፈልገውም ነበር። ይህ ሥርዓት በእርሱ ጉዳይ፣ በመከራዎችና በፈተናዎች መካከል እስከ ሞትም ድረስ ስለ እኛ ፍጹም የሆነውን የሕግ ታዛዥነቱን የወደፊት ቃል ኪዳን ነበር። አርባ ቀናት ሲፈጸሙ ማርያም ለንጽሕናዋ የታዘዙትን መሥዋዕቶች ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደስ ወጣች።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6