ሰቆቃው ኤርምያስ 4

AMHEVGአማርኛ22 ጥቅሶች4:10 አዳምጥ
አዳምጥ 4:10 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1አሌፍ። ወርቁ እንዴት ደበሰ! ጥሩው ወርቅ እንዴት ተለወጠ! የመቅደሱ ድንጋዮች በጐዳና ሁሉ ራስ ተበተኑ።

2ቤት። ጥሩ ወርቅ የሚመስሉ የከበሩ የጽዮን ልጆች፥ የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው እንደ ሸክላ ዕቃ እንዴት ተቈጠሩ!

3ጋሜል። ቀበሮች እንኳ ጡቶታቸውን ገልጠው ግልገሎቻቸውን አጠቡ፤ የወገኔ ልጅ ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጐን ጨካኝ ሆነች።

4ዳሌጥ። ጡት የሚጠባው የሕፃን ምላስ ከጥም የተነሣ ወደ ትናጋው ተጣበቀ፤ ሕፃናት እንጀራ ለመኑ፥ የሚቈርስላቸውም የለም።

5ሄ። የጣፈጠ ነገር ይበሉ የነበሩ በመንገድ ጠፉ፤ በቀይ ግምጃ ያድጉ የነበሩ የፍግ ክምር አቀፉ።

6ዋው። የማንም እጅ ሳይወድቅባት ድንገት ከተገለበጠች፡ ከሰዶም ኃጢአት ይልቅ የወገኔ ሴት ልጅ ኃጢአት በዛች።

7ዛይ። አለቆችዋ ከበረዶ ይልቅ ጥሩ፥ ከወተት ይልቅ ነጭ ነበሩ፤ ገላቸው ከቀይ ዕንቍ ይልቅ ቀይ ነበረ፥ መልካቸውም እንደ ሰንፔር ነበረ።

8ሔት። ፊታቸው ከጥቀርሻ ይልቅ ጠቍሮአል፥ በመንገድም አልታወቁም፤ ቁርበታቸው ወደ አጥንታቸው ተጣብቆአል፤ ደርቆአል፤ እንደ እንጨት ሆኖአል።

9ጤት። በሰይፍ የሞቱ በራብ ከሞቱት ይሻላሉ፤ እነዚህ የምድርን ፍሬ አጥተው ተወግተውም ቀጥነዋል።

10ዮድ። የርኅሩኆች ሴቶች እጆች ልጆቻችውን ቀቅለዋል፤ የወገኔ ሴት ልጅ በመቀጥቀጥዋ መብል ሆኑአቸው።

11ካፍ። እግዚአብሔር መዓቱን ፈጽሞአል፥ ጽኑ ቍጣውን አፍስሶአል፤ እሳትን በጽዮን ውስጥ አቃጠለ፥ መሠረትዋንም በላች።

12ላሜድ። የምድር ነገሥታት በዓለምም የሚኖሩ ሁሉ፡ አስጨናቂና ጠላት በኢየሩሳሌም በር እንዲገባ አላመኑም።

13ሜም። የጻድቃንን ደም በውስጥዋ ስላፈሰሱ፡ ስለ ነቢያቶችዋ ኃጢአትና ስለ ካህናቶች በደል ነው።

14ኖን። ታውረው በመንገድ ላይ ተቅበዘበዙ፤ ልብሳቸው እንዳይዳሰስ በደም ረክሰዋል።

15ሳምኬት። እናንተ ርኩሳን፥ ራቁ፥ ርቃችሁም ሂዱ፥ አትንኩ፡ ብለው ጮኹባቸው። በሸሹና በተቅበዘበዙ ጊዜ፥ በአሕዛብ መካከል፦ በዚህ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖሩም፡ ተባለ።

16ዔ። የእግዚአብሔር ፊት በተናቸው እርሱም ከእንግዲህ ወዲህ አይመለከታቸውም፤ የካህናቱን ፊት አላፈሩም፥ ሽማግሌዎቹንም አላከበሩም።

17ፌ። ዓይናችን ወደ ከንቱ ረዳታችን ገና ሲመለከት ጠፍቶአል፤ በመቆየታችን ማዳን የማይቻለውን ሕዝብ ጠብቀናል።

18ጻዴ። በአደባባያችን እንዳንሄድ ፍለጋችንን ተከተሉ፤ ፍጻሜያችን ቀርቦአል፥ ዕድሜያችን አልቆአል፥ ፍጻሜያችን ደርሶአል።

19ቆፍ። አሳዳጆቻችን ከሰማይ ንስር ይልቅ ፈጣኖች ሆኑ፤ በተራሮች ላይ አሳደዱን፥ በምድረ በዳ ሸመቁብን።

20ሬስ። ስለ እርሱ፦ “በአሕዛብ መካከል በጥላው በሕይወት እንኖራለን፡” ያልነው፡ በእግዚአብሔር የተቀባ፥ የሕይወታችን እስትንፋስ፥ በጕድጓዳቸው ተያዘ።

21ሳን። በዖፅ ምድር የምትኖሪ የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ ሐሤትም አድርጊ፤ ጽዋው ደግሞ ወደ አንቺ ያልፋል፥ አንቺም ትሰክሪአለሽ ትራቈቻለሽም።

22ታው። የጽዮን ልጅ ሆይ፥ የበደልሽ ቅጣት ተፈጸመ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አያስማርክሽም። የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፥ በደልሽን ይቀጣል፤ ኃጢአትሽን ይገልጣል።

ማብራሪያ

4:1-12 እንዴት ያለ ለውጥ ነው እዚህ ያለው! ኃጢአት የላቀውን ኃይልና እጅግ ምርጥ የሆኑ ስጦታዎችን ውበት ያደበዝዛል፤ ነገር ግን በክርስቶስ የሚሰጠን፣ በእሳት የተፈተነ ወርቅ ከእኛ ፈጽሞ አይወሰድም፤ ውጫዊ መልኩ ቢደበዝዝም፣ እውነተኛ ዋጋው ግን ፈጽሞ ሊለወጥ አይችልም። የኢየሩሳሌም የመከበብና የመጥፋት አስፈሪነት እንደገና ተገልጿል። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የኃጢአትን አሳዛኝ ውጤቶች በመመልከት፣ ተመሳሳይ ምክንያቶች አሁን ያለውን ቤተ ክርስቲያንን ወደ ምን እንደሚያወርዷት በቁም ነገር እናስብ። ነገር ግን ጌታ ሆይ፣ በዓመፅ ከአንተ ብንርቅም፣ ወደ እኛ ተመለስ፣ ልባችንንም ወደ አንተ መልስ፣ ስምህንም እንድንፈራ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6