1“አሁን ግን በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱ፥ አባቶቻቸውን ከመንጋዬ ውሾች ጋር ለማኖር የናቅኋቸው፥ በእኔ ላይ ተሳለቁብኝ።
2ሙሉ ሰው መሆናቸው ጠፍቶባቸው ነበርና፡ የእጃቸው ብርታት ለእኔ ምን ይጠቅማል?
3በራብና በቀጠና የመነመኑ ናቸው፤ የመፍረስና የመፈታት ጨለማ ወዳለበት፡ ወደ ምድረ በዳ ይሸሻሉ።
4በቍጥቋጦ አጠገብ ያለውን፡ ጨው ጨው የሚለውን አትክልት ይለቅማሉ፤ የክትክታ ሥር ደግሞ መብላቸው ነው።
5ከሰዎች ተለይተው ተሰደዱ፤ በሌባ ላይ እንደሚጮኽ ይጮኹባቸዋል።
6በሸለቆ ፈረፈርና በምድር ጕድጓድ፡ በድንጋይም ዋሻ ውስጥ ይኖራሉ።
7በቍጥቋጦ መካከል ይጮኻሉ፤ ከሳማ በታች ተሰብስበዋል።
8የሰነፎችና የነውረኞች ልጆች ናቸው፤ ከምድርም በግርፋት የተባረሩ ናቸው።
9“አሁንም እኔ መዝፈኛና መተረቻ ሆንኋቸው።
10ተጸየፉኝ፥ ከእኔም ራቁ፤ አክታቸውንም በፊቴ መትፋትን አልተዉም።
11የቀስቴን አውታር አላልቶብኛል፥ አዋርዶኝማል፤ እነርሱም በፊቴ ልጓማቸውን ፈትተዋል።
12በቀኜ በኩል ዱርዬዎች ተነሥተዋል፥ እግሬንም ይገለብጣሉ፤ የጥፋታቸውን መንገድ በእኔ ላይ ይጐድባሉ።
13ጐዳናዬን ያበላሻሉ፤ ረዳት የሌላቸው ሰዎች መከራዬን ያበዛሉ።
14በሰፊ ፍራሽ እንደሚመጡ ይመጡብኛል፤ በባድማ ውስጥ ይንከባለሉብኛል።
15ድንጋጤ በላዬ ተመለሰችብኝ፥ ክብሬንም እንደ ነፋስ ያሳድዱአታል፤ ደኅንነቴም እንደ ደመና አልፋለች።
16“አሁንም ነፍሴ በውስጤ ፈሰሰች፤ የመከራም ዘመን ያዘችኝ።
17በሌሊት አጥንቴ በደዌ ተነደለች፥ ጅማቶቼም አያርፉም።
18ከታላቁ ደዌ ኃይል የተነሣ ልብሴ ተበላሸች፤ እንደ ቀሚስ ክሳድ አነቀችኝ።
19እርሱ በጭቃ ውስጥ ጣለኝ፥ አፈርና አመድም መሰልሁ።
20“ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አልመለስህልኝም፤ ተነሣሁ፥ አልተመለከትኸኝም።
21ተመልሰህ ጨካኝ ሆንህብኝ፤ በእጅህም ብርታት አስጨነቅኸኝ።
22በነፋስ አነሣኸኝ፥ በላዩም አስቀመጥኸኝ፤ በዐውሎ ነፋስ አቀለጥኸኝ።
23ለሞት ሕያዋንም ሁሉ ለሚሰበሰቡበት ቤት፡ አሳልፈህ እንደምትሰጠኝ አውቄአለሁና።
24“ነገር ግን ሰው በወደቀ ጊዜ እጁን አይዘረጋምን? በጥፋቱስ ጊዜ አይጮኽምን?
25ጭንቅ ቀን ላገኘው ሰው አላለቀስሁምን? ለችግረኛስ ነፍሴ አላዘነችምን?
26ነገር ግን በጎነትን በተጠባበቅሁ ጊዜ ክፉ ነገር መጣችብኝ፤ ብርሃንን በትዕግሥት ጠበቅሁ፥ ጨለማም መጣ።
27አንጀቴ ፈላች፥ አላረፈችም፤ የመከራም ዘመን መጣችብኝ።
28ያለ ፀሐይ በትካዜ ሄድሁ፤ በጉባኤም መካከል ቆሜ ጮኽሁ።
29ለቀበሮ ወንድም፥ ለሰጐንም ባልንጀራ ሆንሁ።
30ቁርበቴ ጠቈረ፥ ከእኔም ተለይቶ እርግፍግፍ አለ፤ አጥንቴም ከትኵሳት የተነሣ ተቃጠለች።
31ስለዚህ መሰንቆዬ ለኀዘን፥ እምቢልታዬም ለሚያለቅሱ ቃል ሆነ።