የዮሐንስ ወንጌል 8

AMHNIVአማርኛ59 ጥቅሶች8:58 አዳምጥ
አዳምጥ 8:58 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ኢየሱስ ግን ወደ ደብረ ዘይት ሄደ።

2በማለዳም በቤተ መቅደስ አደባባይ እንደ ገና ታየ፤ ሕዝቡም በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ሊያስተምራቸውም ተቀመጠ።

3የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን በምንዝር የተያዘች ሴት አመጡ፤ በሕዝቡም ፊት አቁመዋት፣

4ኢየሱስን እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፣ ይህች ሴት ስታመነዝር ተያዘች፤

5ሙሴም፣ እንደዚች ያሉ ሴቶች በድንጋይ እንዲወገሩ በሕጉ አዞናል፤ አንተስ ምን ትላለህ?”

6ይህን ጥያቄ ያቀረቡለት፣ እርሱን የሚከሱበት ምክንያት ለማግኘት ሲፈትኑት ነው። ኢየሱስ ግን ጎንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ይጽፍ ጀመር።

7በጥያቄ ሲወተውቱት ቀና ብሎ፣ “ከእናንተ ኀጢአት የሌለበት እርሱ አስቀድሞ ድንጋይ ይወርውርባት” አላቸው።

8እንደ ገናም ጎንበስ ብሎ በምድር ላይ ጻፈ።

9ይህን እንደ ሰሙ፣ ከሽማግሌዎች ጀምሮ አንድ በአንድ ወጡ፤ ሴትዮዋም እዚያው ፊቱ እንደ ቆመች ኢየሱስ ብቻውን ቀረ።

10ኢየሱስም ቀና ብሎ፣ “አንቺ ሴት፣ ሰዎቹ የት ሄዱ? የፈረደብሽ የለምን?” አላት።

11እርሷም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድም የለም” አለች። ኢየሱስም፣ “እኔም አልፈርድብሽም፤ በይ ሂጂ፤ ከእንግዲህ ግን ኀጢአት አትሥሪ” አላት።

12ኢየሱስ እንደ ገና ለሰዎቹ፣ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝም የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ ከቶ በጨለማ አይመላለስም” አላቸው።

13ፈሪሳውያንም፣ “አንተ ስለ ራስህ ስለምትመሰክር፣ ምስክርነትህ ተቀባይነት የለውም” አሉት።

14ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ከየት እንደ መጣሁና ወዴት እንደምሄድ ስለማውቅ ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከየት እንደ መጣሁ ወይም ወዴት እንደምሄድ የምታውቁት ነገር የለም።

15እናንተ እንደ ሰው አስተሳሰብ ትፈርዳላችሁ፤ እኔ በማንም አልፈርድም፤

16ብፈርድም፣ ከላከኝ ከአብ ጋር እንጂ ብቻዬን ስላልሆንሁ ፍርዴ ትክክል ነው።

17የሁለት ሰዎች ምስክርነት ተቀባይነት እንዳለው በሕጋችሁ ተጽፎአል።

18ስለ ራሴ የምመሰክር አንዱ እኔ ነኝ፤ ሌላውም ምስክሬ የላከኝ አብ ነው።”

19ከዚያም፣ “አባትህ የት ነው?” አሉት። ኢየሱስም፣ “አባቴንም እኔንም አታውቁም፤ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ፣ አባቴንም ባወቃችሁ ነበር” ሲል መለሰላቸው።

20ኢየሱስ ይህን የተናገረው በቤተ መቅደሱ ግቢ፣ በግምጃ ቤት አጠገብ ሲያስተምር ነበር፤ ይሁን እንጂ ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም።

21ኢየሱስም እንደ ገና፣ “እኔ እሄዳለሁ፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ በኀጢአታችሁም ትሞታላችሁ፤ እኔ ወደምሄድበት ግን ልትመጡ አትችሉም” አላቸው።

22አይሁድም፣ “ ‘እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ ያለው ራሱን ሊገድል ይሆን?” አሉ።

23እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ከታች ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፤ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም።

24በኀጢአታችሁ እንደምትሞቱ ነግሬአችኋለሁ፤ እኔ እርሱ ነኝ ስላችሁ እኔ እርሱ እንደሆንሁ ካላመናችሁ፣ በኀጢአታችሁ ትሞታላችሁና።”

25እነርሱም፣ “ለመሆኑ፣ አንተ ማን ነህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እስካሁን የነገርኋችሁ እኔ እርሱ ነኝ፤

26በእናንተ ላይ ብዙ የምናገረውና ብዙ የምፈርደው ነገር አለኝ፤ ዳሩ ግን የላከኝ ታማኝ ነው፤ ከእርሱም የሰማሁትን ለዓለም እናገራለሁ።”

27እነርሱም ስለ አብ እየነገራቸው እንደ ነበር አላስተዋሉም።

28ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰው ልጅን ከፍ ከፍ ባደረጋችሁት ጊዜ፣ ያ ያልሁት እርሱ እኔ እንደሆንሁና አብ ያስተማረኝን እንደምናገር፣ በራሴም ፈቃድ ምንም እንደማላደርግ ታውቃላችሁ፤

29የላከኝ እርሱ ከእኔ ጋር ነው፤ ምንጊዜም የሚያስደስተውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም።”

30ይህንም እንደ ተናገረ ብዙዎች በእርሱ አመኑ።

31ኢየሱስም በእርሱ ያመኑትን አይሁድ እንዲህ አላቸው፤ “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤

32እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል።”

33እነርሱም መልሰው፣ “እኛ የአብርሃም ልጆች ነን፤ ለማንም ባሪያዎች ሆነን አናውቅም፤ ታዲያ፣ ‘ነጻ ትወጣላችሁ’ እንዴት ትለናለህ?” አሉት።

34ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ኀጢአት የሚያደርግ የኀጢአት ባሪያ ነው፤

35ባሪያ ለዘለቄታ በቤተ ሰቡ ውስጥ አይኖርም፤ ልጅ ግን ምንጊዜም በቤት ይኖራል።

36እንግዲህ ወልድ ነጻ ካወጣችሁ፣ በእውነት ነጻ ትሆናላችሁ።

37የአብርሃም ልጆች መሆናችሁን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ቃሌን ስለማትቀበሉ ልትገድሉኝ ቈርጣችሁ ተነሥታችኋል።

38እኔ በአባቴ ዘንድ ያየሁትን እናገራለሁ፤ እናንተም ከአባታችሁ የሰማችሁትን ታደርጋላችሁ።”

39እነርሱም፣ “አባታችንስ አብርሃም ነው” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የአብርሃም ልጆችስ ብትሆኑ፣ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር።

40ከእግዚአብሔር ሰምቼ እውነቱን የነገርኋችሁን እኔን ለመግደል ቈርጣችሁ ተነሥታችኋል፤ አብርሃም ግን እንዲህ አላደረገም።

41እናንተ የምታደርጉት አባታችሁ የሚያደርገውን ነው።” እነርሱም፣ “እኛስ በዝሙት የተወለድን አይደለንም፤ አባታችንም አንዱ እግዚአብሔር ብቻ ነው” ሲሉ መለሱለት።

42ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር አባታችሁ ቢሆን ኖሮ፣ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፣ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እርሱ ላከኝ እንጂ በገዛ ራሴ አልመጣሁም።

43የምናገረውን ለምን አታስተውሉም? ምክንያቱም ቃሌን መስማት ስለማትችሉ ነው።

44እናንተ የአባታችሁ የዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት ለመፈጸም ትሻላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ በእርሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት አልጸናም፤ እርሱ ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት በመሆኑ ሐሰትን ሲናገር፣ የሚናገረው ከራሱ አፍልቆ ነው፤

45እኔ ግን እውነት ስለምናገር አታምኑኝም።

46ከእናንተ ስለ ኀጢአት በማስረጃ ሊከሰኝ የሚችል አለን? እውነት የምናገር ከሆነ፣ ለምን አታምኑኝም?

47ከእግዚአብሔር የሆነ እግዚአብሔር የሚለውን ይሰማል፤ እናንተ ግን ከእግዚአብሔር ስላልሆናችሁ አትሰሙም።”

48አይሁድም መልሰው፣ “አንተ ሳምራዊ ነህ፤ ደግሞም ጋኔን አድሮብሃል ማለታችን ትክክል አይደለምን?” አሉት።

49ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔስ አባቴን አከብረዋለሁ እንጂ ጋኔን አላደረብኝም፤ እናንተ ግን ታዋርዱኛላችሁ።

50እኔ የራሴን ክብር አልፈልግም፤ የሚፈልግ ግን አለ፤ ፈራጁም እርሱ ነው።

51እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ቃሌን ቢጠብቅ፣ ሞትን ፈጽሞ አያይም።”

52አይሁድም እንዲህ አሉት፤ “ጋኔን እንዳለብህ አሁን ዐወቅን፤ አብርሃም ሞተ፤ ነቢያትም እንዲሁ፤ አንተ ግን ማንም ቃልህን ቢጠብቅ ሞትን ፈጽሞ እንደማይቀምስ ትናገራለህ።

53አንተ ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? እርሱ ሞተ፤ ነቢያቱም እንዲሁ፤ ለመሆኑ አንተ ማን ነኝ ልትል ነው?”

54ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ ራሴን ባከብር፣ ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ ግን እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው።

55እናንተ ባታውቁትም እኔ ዐውቀዋለሁ፤ አላውቀውም ብል፣ እኔም እንደ እናንተው ሐሰተኛ እሆናለሁ። እኔ ግን ዐውቀዋለሁ፤ ቃሉንም እጠብቃለሁ።

56አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ለማየት ተስፋ በማድረግ ተደሰተ፤ አየም፤ ሐሤትም አደረገ።”

57አይሁድም፣ “ገና አምሳ ዓመት ያልሞላህ፣ አንተ አብርሃምን አይተሃል!” አሉት።

58ኢየሱስም፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ፣ እኔ ነኝ” አላቸው።

59በዚህን ጊዜ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወረባቸው፤ ከቤተ መቅደስም ወጥቶ ሄደ።

ማብራሪያ

ዮሐንስ 8:1-11 ክርስቶስ ሕግን አልወቀሰም፣ የእስረኛዋንም ጥፋት አላቀለለም፤ የፈሪሳውያንም አስመሳይ ቅንዓት አልደገፈም። ሌሎችን እየፈረዱ እነርሱ ራሳቸው ግን ያንኑ ነገር የሚያደርጉ በራሳቸው የተወገዙ ናቸው። የሌሎችን ስህተቶች ለመውቀስ በየትኛውም መንገድ የተጠሩ ሁሉ፣ ራሳቸውን እንዲመረምሩና ንጹህ ሆነው ራሳቸውን እንዲጠብቁ በተለይ ሊጠነቀቁ ይገባል። በዚህ ጉዳይ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣበትን ታላቅ ሥራ አከናወነ፤ እርሱም ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ መጥራት፣ ሊያጠፋ ሳይሆን ሊያድን ነበር። እርሱ ዓላማው የተከሰሰችውን ሴት ብቻ ሳይሆን፣ ምሕረቱን በማሳየት ንስሐ እንድትገባ ማድረግ ነበር፤ ከሳሾቹንም ደግሞ ኃጢአቶቻቸውን በማሳየት ንስሐ እንዲገቡ ማድረግ ነበር። እነርሱ ሊያጠምዱት አስበው ነበር፤ እርሱ ግን ሊያሳምናቸውና ሊመልሳቸው ፈለገ። በፍርድ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ከመግባት ተቆጠበ። ብዙ ወንጀሎች ከሚያገኙት እጅግ የከፋ ቅጣት ይገባቸዋል፤ እኛ ግን ያልተጠራንበትን ሥራ በራሳችን ላይ ለመውሰድ የገዛ ሥራችንን መተው የለብንም። ክርስቶስ በሰደዳት ጊዜ በዚህ ማስጠንቀቂያ ነበር፦ "ሂጂ፣ ከእንግዲህም ወዲያ ዳግመኛ ኃጢአት አትሥሪ።" የወንጀለኛን ሕይወት ለማዳን የሚረዱ፣ በዚሁ ጥንቃቄ ነፍስንም ለማዳን መርዳት አለባቸው። ክርስቶስ የማይኮንናቸው በእውነት ደስተኞች ናቸው። ክርስቶስ ያለፉትን ኃጢአቶቻችንን በመሰረይቱ ያሳየን ሞገስ፣ እኛን "ሂዱ፣ ከእንግዲህም ወዲያ ኃጢአት አትሥሩ" በሚለው ቃል ሊያነሳሳን ይገባል።

8:12-16 ክርስቶስ የዓለም ብርሃን ነው። እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ክርስቶስም የማይታየው የእግዚአብሔር ምስል ነው። አንድ ፀሐይ ዓለሙን በሙሉ እንደምታበራ፣ እንዲሁ አንድ ክርስቶስ ያበራል፤ ከዚህ በላይም አያስፈልግም። ፀሐይ ባይኖር ዓለም እንዴት ያለ ጨለማ ወህኒ ቤት ትሆን ነበር! እንዲሁ ኢየሱስ ባይኖር ትሆን ነበር፤ ብርሃንም በእርሱ ወደ ዓለም ገባ። ክርስቶስን የሚከተሉ በጨለማ አይመላለሱም። ከሚያጠፋ ስህተት ሊጠብቋቸው የሚያስፈልጉ እውነቶች አይጎድሏቸውም፤ ከሚያወግዝ ኃጢአት ሊጠብቋቸው የሚያስፈልጉ የሃይማኖት ግዴታ መንገድ መመሪያዎችም አይጎድሏቸውም።

፰፡፲፯-፳ ክርስቶስን ይበልጥ ብናውቅ፣ አብን ይበልጥ እናውቅ ነበር። ክርስቶስን ለመማር ፈቃደኞች ያልሆኑ ሰዎች፣ ስለ እግዚአብሔር ያላቸው ግምቶች ከንቱ ይሆናሉ። ክብሩንና ጸጋውን የማያውቁት፣ የላከውን አብ አያውቁትም። ከዓለም የምንለይበት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ የተመካ ነው። ጠላቶቻችን ቀድመው ሊያፋጥኑት አይችሉም፣ ወዳጆቻችንም አብ ከወሰነው ጊዜ በላይ ሊያዘገዩት አይችሉም። እያንዳንዱ እውነተኛ አማኝ ቀና ብሎ በደስታ "ዘመኔ በእጅህ ነው፣ በራሴ እጅ ከሚሆን ይልቅ በአንተ እጅ ይሻላል" ብሎ መናገር ይችላል። ለእግዚአብሔር ዓላማዎች ሁሉ ጊዜ አለው።

8:21-29 በማያምንነት ውስጥ የኖሩና በማያምንነት የሞቱ ሰዎች ለዘላለም ይጠፋሉ። አይሁዶች የዚህ ዘመን የክፉ ዓለም ሰዎች ነበሩ፤ ኢየሱስ ግን የሰማያዊና የመለኮታዊ ባሕርይ ባለቤት በመሆኑ ትምህርቱ፣ መንግሥቱና በረከቶቹ የሚስማማቸው አልነበረም። ነገር ግን የወንጌል ጸጋ ለተገዙ ሁሉ የሕግ እርግማን ተወግዷል። ከክርስቶስ ጸጋ ትምህርት በቀር ከኃጢአት ወደ እግዚአብሔር ሊመልሰን በቂ ኃይል ያለው ክርክር ሊሆን የሚችል ሌላ ምንም የለም፤ ከክርስቶስ ጸጋ መንፈስ በቀርም በቂ ኃይል ያለው አስፈጻሚ ሊሆን የሚችል ሌላ ማንም የለም። ያ መንፈስም ሆነ ያ ትምህርት በክርስቶስ በሚያምኑት ላይ ብቻ ለመሥራት ተሰጥተዋል። አንዳንዶች፡- “ይህ ኢየሱስ ማነው?” ይላሉ። እርሱ ነቢይ፣ እጅግ በጣም ጥሩ አስተማሪና ከፍጥረትም በላይ እንደሆነ ይቀበላሉ፤ ነገር ግን ከሁሉ በላይ እንደሆነ፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም የተባረከ አምላክ እንደሆነ ሊቀበሉት አይችሉም። ይህ አይበቃም? ኢየሱስ እዚህ ለጥያቄው መልስ ይሰጣል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6