ትንቢተ ኤርምያስ 22

AMHEVGአማርኛ30 ጥቅሶች5:39 አዳምጥ
አዳምጥ 5:39 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ቤት ውረድ በዚያም ይህን ቃል ተናገር፥

2እንዲህም በል፦ በዳዊት ዙፋን የምትቀመጥ የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ አንተና ባሪያዎችህ በእነዚህም በሮች የሚገባ ሕዝብህ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

3እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ የተበዘበዘውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ፤ መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም አትበድሉ፥ አታምፁባቸውም፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን አታፍስሱ።

4ይህንንም ነገር ብታደርጉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡ ነገሥታት፥ በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ ተቀምጠው፥ በዚህ ቤት በሮች ይገባሉ፤ እርሱም ባሪያዎቹም ሕዝቡም እንዲሁ ይገባሉ።

5ነገር ግን ይህን ቃል ባትሰሙ፥ ይህ ቤት ወና እንዲሆን በራሴ ምያለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

6እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ቤት እንዲህ ይላልና፦ አንተ በእኔ ዘንድ እንደ ገለዓድና እንደ ሊባኖስ ራስ ነህ፥ ነገር ግን በእርግጥ ምድረ በዳ ማንም የማይቀመጥባቸውም ከተሞች አደርግሃለሁ።

7መሣሪያም የሚይዙትን አጥፊዎች በአንተ ላይ አዘጋጃለሁ፥ የተመረጡትንም የዝግባ ዛፎችህን ይቈርጣሉ፥ በእሳትም ውስጥ ይጥሉአቸዋል።

8ብዙ አሕዛብም በዚህች ከተማ አጠገብ ያልፋሉ፥ ሁሉም ባልንጀሮቻቸውን፦ እግዚአብሔር በዚህች ታላቅ ከተማ ለምን እንዲህ አደረገ? ይላሉ።

9እነርሱም፦ የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ትተው ለሌሎች አማልክት ስለ ሰገዱ ስላመለኩአቸውም ነዋ፡ ብለው ይመልሳሉ።

10ከእንግዲህ ወዲህ አይመለስምና፥ የተወለደባትንም አገር አያይምና ለሚወጣ እጅግ አልቅሱ እንጂ ለሞተ አታልቅሱ አትዘኑለትም።

11በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ ስለ ነገሠው ከዚህም ስፍራ ስለ ወጣው ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ሰሎም እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦

12እንግዲህም ወደዚህ አይመለስም፥ በተማረከባት አገር ይሞታል እንጂ፤ ይህችንም አገር ከእንግዲህ ወዲህ አያይም።

13ቤቱን በግፍ ሰገነቱንም በዓመፅ ለሚሠራ፥ ባልንጀራውንም እንዲያው በከንቱ ለሚያሠራ፥ ዋጋውንም ለማይሰጠው፤

14ለራሴ ሰፊ ቤት ትልቅም ሰገነት እሠራለሁ ለሚል፥ መስኮትንም ለሚያወጣ፥ በዝግባም ሥራ ለሚያስጌጥ፥ በቀይ ቀለምም ለሚቀባው ወዮለት!

15በዝግባ እንጨት ስለምትወዳደር በውኑ ትነግሣለህን? በውኑ አባትህ አይበላምና አይጠጣም ነበርን? ፍርድንና ጽድቅንስ አያደርግም ነበርን? በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖለት ነበር።

16የድሀውንና የችግረኛውን ፍርድ ይፈርድ ነበር፥ በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖ ነበር። ይህ እኔን ማወቅ አይደለምን? ይላል እግዚአብሔር።

17ዓይንህና ልብህ ግን ለስስት ንጹሕ ደምንም ለማፍሰስ ዓመፅንና ግፍንም ለመሥራት ብቻ ነው።

18ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮስያስ ልጅ ስለ ኢዮአቄም እንዲህ ይላል፦ ወንድሜ ሆይ፥ ወዮ! እያሉ አያለቅሱለትም፥ ወይም፦ ጌታ ሆይ፥ ወዮ! እያሉ አያለቅሱለትም።

19አህያም እንደሚቀበር ይቀበራል፥ ከኢየሩሳሌምም በር ወደ ውጭ ተጐትቶ ይጣላል።

20ውሽሞችሽ ሁሉ ጠፍተዋልና ወደ ሊባኖስ ወጥተሽ ጩኺ፤ በባሳን ላይ ድምፅሽን አንሺ፤ በዓባሪምም ውስጥ ሆነሽ ጩኺ።

21በደኅንነትሽ ጊዜ ተናገርሁሽ፤ አንቺም፦ አልሰማም፡ አልሽ። ከሕፃንነትሽ ጀምሮ ቃሌን አለመስማትሽ መንገድሽ ነው።

22በግ ጠባቂዎችሽን ሁሉ ነፋስ ይጠብቃቸዋል፥ ውሽሞችሽም ተማርከው ይሄዳሉ፤ በዚያን ጊዜም ስለ ክፋትሽ ሁሉ ታፍሪያለሽ ትጐሳቈይማለሽ።

23አንቺ በሊባኖስ የምትቀመጪ፥ በዝግባ ዛፍም ውስጥ ጎጆሽን የምትሠሪ ሆይ፥ ምጥ እንደ ያዛት ሴት ሕማም በያዘሽ ጊዜ እንዴት ታጓሪያለሽ!

24እኔ ሕያው ነኝና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጅ ኢኮንያን የቀኝ እጄ ማኅተም ቢሆን ኖሮ እንኳ፥ ከዚያ እነቅልህ ነበር፥ ይላል እግዚአብሔር፤

25ነፍስህንም ለሚሹት ለምትፈራቸውም እጅ፥ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ለከለዳውያንም እጅ እሰጥሃለሁ።

26አንተንም የወለደችህንም እናትህን ወዳልተወለዳችሁባት ወደ ሌላ አገር እጥላችኋለሁ፥ በዚያም ትሞታላችሁ።

27ይመለሱባትም ዘንድ ነፍሳቸው ወደምትመኛት ወደዚያች ምድር አይመለሱም።

28በውኑ ይህ ሰው ኢኮንያን የተናቀና የተሰበረ የሸክላ ዕቃ ነውን? ወይስ እርሱ ለአንዳች የማይረባ የሸክላ ዕቃ ነውን? እርሱና ዘሩስ በማያውቋት ምድር ስለ ምን ተጥለው ወደቁ?

29ምድር ሆይ፥ ምድር ሆይ፥ ምድር ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ።

30እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከዚህ ሰው ዘር የሚከናወን በዳዊትም ዙፋን ላይ የሚቀመጥ በይሁዳም የሚነግሥ እንግዲህ አይገኝምና፦ መካን በዘመኑም የማይከናወንለት ሰው፡ ብላችሁ ጻፉ።

ማብራሪያ

፳፪፥፩-፱ የይሁዳ ንጉሥ በዳዊት ዙፋን ላይ እንደተቀመጠ፣ እንደ እግዚአብሔር ልብ የሆነውም ሰው ተብሎ ተጠቅሷል። እርሱም ምሳሌውን ይከተል ዘንድ፣ ለእርሱ የተሰጡት የተስፋ ቃሎች ጥቅም እንዲያገኝ። መንግሥትን ለመጠበቅ መንገድ የኃላፊነቱን ሥራ መወጣት ነው። ኃጢአት ግን የነገሥታትን ቤቶች ጥፋት እንደሚያመጣ፣ እንደዚሁም ደግሞ የተራ ሰዎችንም ያጠፋል። እግዚአብሔር ካዘጋጃቸው አጥፊዎች ጋር ማን ሊፋለም ይችላል? እግዚአብሔር ሰዎችንም፣ ከተማዎችንም ሆነ ብሔሮችን የሚያጠፋው ከኃጢአት በቀር አይደለም፤ በዚህ ዓለምም እንኳ ብዙ ጊዜ ለምን ወንጀሎች ቅጣት እንደላከ ግልጽ ያደርጋል፤ በፍርድ ቀንም ግልጽ ይሆናል።

22:10-19 እዚህ ጋር እጅግ አምላክን የሚፈራ አባት ክፉ ልጆች በሆኑ በሁለት ነገሥታት ላይ የሞት ፍርድ ተላልፏል። ኢዮስያስ በዚህ ዓለም የሚመጣውን ክፉ ነገር ከማየት ተከልክሏል፣ በሌላውም ዓለም የሚመጣውን መልካም ነገር ለማየት ተወስዷል፤ ስለዚህም ስለ እርሱ አታልቅሱ፣ ነገር ግን አስከፊ ምርኮኛ ሆኖ ይኖርና ይሞታል ተብሎ ለሚገመተው ልጁ ለሰሉብ አልቅሱ። የሚሞቱ ቅዱሳን በትክክል የሚቀኑባቸው ሲሆኑ፣ በሕይወት ያሉ ኃጢአተኞች ግን በትክክል የሚያሳዝኑ ናቸው። እዚህም ደግሞ የኢዮአቄም ዕጣ ፈንታ ተቀምጧል። መሳፍንትና ታላላቅ ሰዎች ቤቶችን እንዲሠሩ፣ እንዲያሳምሩና የቤት ዕቃዎችን እንዲያስገቡ ሕጋዊ መሆኑ ጥርጥር የለውም፤ ነገር ግን ቤቶቻቸውን የሚያሰፉና ዕጹብ ድንቅ የሚያደርጉ ሰዎች ከከንቱ ውዳሴ ሥራዎች በጥንቃቄ ሊጠብቁ ይገባል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6