ትንቢተ ኢሳይያስ 20

AMHEVGአማርኛ6 ጥቅሶች1:12 አዳምጥ
አዳምጥ 1:12 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1የአሦር ንጉሥ ሳርጎን ተርታንን በሰደደ ጊዜ እርሱም ወደ አዛጦን በመጣ ጊዜ አዛጦንም ወግቶ በያዛት ጊዜ፥

2በዚያ ዓመት እግዚአብሔር የአሞጽን ልጅ ኢሳይያስን፦ ሂድ፥ ማቅህን ከወገብህ አውጣ፥ ጫማህንም ከእግርህ አውልቅ፡ ብሎ ተናገረው። እንዲህም አደረገ፥ ራቁቱንም ባዶ እግሩንም ሄደ።

3እግዚአብሔርም አለ፦ ባሪያዬ ኢሳይያስ በግብፅና በኢትዮጵያ ላይ ሦስት ዓመት ለምልክትና ለተአምራት ሊሆን ራቁቱንና ባዶ እግሩን እንደ ሄደ፥

4እንዲሁ የአሦር ንጉሥ የግብፅንና የኢትዮጵያን ምርኮ፥ ጐበዛዝቱንና ሽማግሌዎቹን፥ ራቁታቸውንና ባዶ እግራቸውን አድርጎ ገላቸውንም ገልጦ፥ ለግብፅ ጕስቍልና ይነዳቸዋል።

5እነርሱም ከተስፋቸው ከኢትዮጵያ ከትምክሕታቸውም ከግብፅ የተነሣ ይፈራሉ ያፍሩማል፤

6በዚያም ቀን በዚች ባሕር ዳርቻ የሚቀመጡ፦ እነሆ፥ ከአሦር ንጉሥ እንድን ዘንድ ለእርዳታ ወደ እነርሱ የሸሸንበት ተስፋችን ይህ ነበረ፤ እኛስ እንዴት እናመልጣለን? ይላሉ።

ማብራሪያ

20:1-6 የግብፅና የኢትዮጵያ ወረራና ድል መንሳት። ኢሳይያስ በውጭ ሲመላለስ ባልተለመደው ልብሱ ለሕዝቡ ምልክት ነበር። እርሱ እንደ ነቢይ ለዓለም እንደሞተ ለማሳየት በተለምዶ ማቅ ይለብስ ነበር። ይህንንም ከወገቡ መፍታት፣ የላይኛውን ልብስ አለመልበስ፣ ባዶ እግሩንም መሄድ ነበረበት። ይህ ምልክት የሚያመለክተውም ግብፃውያንና ኢትዮጵያውያን እንዲህ ተራቁተው በአሦር ንጉሥ ተማርከው እንደሚወሰዱ ነበር። ዓለም ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ልዩ ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ አማኞችን ሞኞች አድርጋ ትመለከታለች።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6