1የአሦር ንጉሥ ሳርጎን ተርታንን በሰደደ ጊዜ እርሱም ወደ አዛጦን በመጣ ጊዜ አዛጦንም ወግቶ በያዛት ጊዜ፥
2በዚያ ዓመት እግዚአብሔር የአሞጽን ልጅ ኢሳይያስን፦ ሂድ፥ ማቅህን ከወገብህ አውጣ፥ ጫማህንም ከእግርህ አውልቅ፡ ብሎ ተናገረው። እንዲህም አደረገ፥ ራቁቱንም ባዶ እግሩንም ሄደ።
3እግዚአብሔርም አለ፦ ባሪያዬ ኢሳይያስ በግብፅና በኢትዮጵያ ላይ ሦስት ዓመት ለምልክትና ለተአምራት ሊሆን ራቁቱንና ባዶ እግሩን እንደ ሄደ፥
4እንዲሁ የአሦር ንጉሥ የግብፅንና የኢትዮጵያን ምርኮ፥ ጐበዛዝቱንና ሽማግሌዎቹን፥ ራቁታቸውንና ባዶ እግራቸውን አድርጎ ገላቸውንም ገልጦ፥ ለግብፅ ጕስቍልና ይነዳቸዋል።
5እነርሱም ከተስፋቸው ከኢትዮጵያ ከትምክሕታቸውም ከግብፅ የተነሣ ይፈራሉ ያፍሩማል፤
6በዚያም ቀን በዚች ባሕር ዳርቻ የሚቀመጡ፦ እነሆ፥ ከአሦር ንጉሥ እንድን ዘንድ ለእርዳታ ወደ እነርሱ የሸሸንበት ተስፋችን ይህ ነበረ፤ እኛስ እንዴት እናመልጣለን? ይላሉ።