ትንቢተ ሆሴዕ 6

AMHEVGአማርኛ11 ጥቅሶች1:39 አዳምጥ
አዳምጥ 1:39 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል።

2ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፥ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን።

3እንወቅ፤ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል፤ እንደ ወገግታም ተዘጋጅቶ እናገኘዋለን፤ እንደ ዝናብም ምድርንም እንደሚያጠጣ እንደ መጨረሻ ዝናብ ይመጣል።

4ምሕረታችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ጠል ነውና ኤፍሬም ሆይ፥ ምን ላድርግልህ? ይሁዳ ሆይ፥ ምን ላድርግልህ?

5ስለዚህ በነቢያት እጅ ቈረጥኋቸው፥ በአፌም ቃል ገደልኋቸው፤ ፍርዴም እንደ ብርሃን ይወጣል።

6ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለሁና።

7እነርሱ ግን እንደ አዳም ቃል ኪዳንን ተላልፈዋል፤ በዚያም ላይ ወንጅለውኛል።

8ገለዓድ ኃጢአትን የሚሠሩ ሰዎች ከተማ፥ በደምም የተቀባ ነው።

9ለሰውም እንደሚያደቡ ወንበዴዎች፥ እንዲሁ የካህናት ወገኖች በሴኬም መንገድ ላይ ይገድላሉ፤ ሴሰኝነትንም ያደርጋሉ።

10በእስራኤል ቤት የሚያስፈራን ነገር አይቻለሁ፤ በዚያ በኤፍሬም ውስጥ ግልሙትና ተገኘ፥ እስራኤልም ረክሶአል።

11ይሁዳ ሆይ፥ የሕዝቤን ምርኮ በምመልስበት ጊዜ ለአንተ ደግሞ መከር ተወስኖልሃል።

ማብራሪያ

6:1-3 ከእግዚአብሔር በፍቃደኝነትና በአንድነት ርቀው፣ አንዱ ሌላውን ወደ ኃጢአት ያሳሳቱት፣ በፍቃደኝነትና በአንድነት ወደ እርሱ መመለስ ይገባቸዋል፤ ይህም ለክብሩና ለጥቅማቸው ይሆናል። በመከራ ውስጥ ለመጽናት፣ ንስሐችንንም ለማበረታታት፣ ስለ እግዚአብሔር እንዲሁም ስለ እኛ ስላለው ዓላማውና እቅዱ መልካም ሀሳቦችን መጠበቅ እጅግ ጠቃሚ ይሆናል። ከመከራ መዳን ለእነርሱ እንደ ከሙታን ሕይወት ሊሆን ይገባል። እግዚአብሔር ያድሳቸዋል፤ የዚህ ማረጋገጫ ወደ እርሱ እንዲመለሱ ሊያነሳሳቸው ይገባል። ነገር ግን ይህ የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤ የበለጠ የሚያመለክት ይመስላል። ነቢዩ የቤተ ክርስቲያንን ከመከራዋ መዳን በትንቢት በነገረ ጊዜ፣ በክርስቶስ ያለንን መዳን መጠቆሙን፤ አሁን ደግሞ እነዚህ ቃላት በክርስቶስ ትንሳኤ ሲፈጸሙ፣ የሚመጣው እርሱ መሆኑንና ሌላም መጠበቅ እንደሌለብን እምነታችንን የሚያጸና የእግዚአብሔርን ጥበብና መልካምነት እናድንቅ። እዚህ ላይ የከበረ በረከት ተስፋ ተሰጥቷል፤ ይህም እግዚአብሔርን ማወቅ የሆነው የዘላለም ሕይወት ነው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6