የሐዋርያት ሥራ 2

AMHNIVአማርኛ47 ጥቅሶች7:28 አዳምጥ
አዳምጥ 7:28 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1የበዓለ ኀምሳ ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድነት፣ በአንድ ስፍራ ተሰብስበው ነበር፤

2ድንገትም እንደ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጥቶ ተቀምጠው የነበሩበትን ቤት እንዳለ ሞላው።

3የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፉ።

4ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስም እንዲናገሩ በሰጣቸው መጠን በሌሎች ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር።

5በዚህ ጊዜ ከሰማይ በታች ካለው ሕዝብ ሁሉ የመጡና እግዚአብሔርን የሚፈሩ አይሁድ በኢየሩሳሌም ነበሩ።

6ይህን ድምፅ ሲሰሙ፣ ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ እያንዳንዱም ሰው፣ ሰዎቹ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ፤

7በመገረምና በመደነቅም እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ የሚነጋገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን?

8ታዲያ፣ እያንዳንዳችን በተወለድንበት፣ በራሳችን ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማቸው እንዴት ቢሆን ነው?

9እኛ የጳርቴና፣ የሜድ፣ የኢላሜጤም ሰዎች፣ በመስጴጦምያ፣ በይሁዳ፣ በቀጶዶቅያ፣ በጳንጦስ፣ በእስያ፣

10በፍርግያ፣ በጵንፍልያ፣ በግብፅ፣ በቀሬና አጠገብ ባሉት በሊቢያ አውራጃዎች የምንኖር፣ ከሮም የመጣን

11አይሁድና ወደ ይሁዲነት የገባን፣ የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች ስንሆን፣ ሰዎቹ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን!”

12ሁሉም በአድናቆትና ግራ በመጋባት፣ “ይህ ነገር ምን ይሆን?” ተባባሉ።

13አንዳንዶቹ ደግሞ “ያልፈላ ብዙ የወይን ጠጅ ጠጥተዋል” በማለት አፌዙባቸው።

14በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋር ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተናገረ፤ “እናንት የይሁዳ ሰዎች፤ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፤ ይህን አንድ ነገር ዕወቁ፤ በጥሞናም አድምጡ።

15ጊዜው ገና ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ስለ ሆነ፣ እናንተ እንደምታስቡት እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም።

16ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል እንዲህ ተብሎ የተነገረ ነው፤

17“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመጨረሻው ቀን፣ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጒልማሶቻችሁ ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁ ሕልም ያልማሉ።

18በዚያ ጊዜ በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ፣ መንፈሴን አፈሳለሁ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ።

19በላይ በሰማያት ድንቅ ነገሮችን፣ አሳያለሁ፤ በታች በምድርም ምልክቶችን እሰጣለሁ፤ ደምና እሳት፣ የጢስም ጭጋግ ይሆናል።

20ታላቅና ክቡር የሆነው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ፀሓይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ።

21የጌታን ስም፣ የሚጠራ ሁሉ ይድናል።’

22“የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ይህን ቃል ስሙ፤ እናንት ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ታምራትን፣ ድንቅ ነገሮችንና ምልክቶችን በእርሱ በኩል በማድረግ ለናዝሬቱ ኢየሱስ መስክሮለታል።

23እግዚአብሔር በጥንት ውሳኔውና በቀደመው ዕውቀቱ ይህን ሰው አሳልፎ በእጃችሁ ሰጣችሁ፤ እናንተም በክፉ ሰዎች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት።

24እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አስወግዶ አስነሣው፤ ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለምና።

25ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ ይላል፤ “ ‘ጌታን ሁል ጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እርሱ በቀኜ ነውና፣ ከቶ አልታወክም።

26ስለዚህ ልቤ ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ፤ ሥጋዬም በተስፋ ይኖራል።

27ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤ ቅዱስህም መበስበስን እንዲያይ አታደርግም።

28የሕይወትን መንገድ እንዳውቅ አደረግኸኝ፤ በፊትህም በሐሤት ትሞላኛለህ።’

29“ወንድሞች ሆይ፤ ከቀደምት አባቶች ዳዊት ሞቶ እንደ ተቀበረ፣ መቃብሩም እስከ ዛሬ ድረስ በመካከላችን እንደሚገኝ በድፍረት መናገር እችላለሁ።

30ነቢይ በመሆኑም፣ እግዚአብሔር ከዘሮቹ አንዱን በዙፋኑ ላይ እንደሚያስቀምጥ በመሐላ ቃል የገባለት መሆኑን ዐወቀ።

31ይህንን አስቀድሞ በማየቱ እርሱ በሲኦል እንደማይቀርና ሥጋውም እንደማይበሰብስ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ተናገረ።

32ይህን ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን።

33ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ካለ በኋላ፣ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ተቀብሎ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።

34ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣም፤ እርሱ ራሱ ግን እንዲህ ብሎአል፤ “ ‘ጌታ ጌታዬን፣

35“ጠላቶችህን ለእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ” አለው።’

36“እንግዲህ፣ እግዚአብሔር ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን፣ ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ ይረዳ!”

37ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ ልባቸው እጅግ ተነካ፤ ጴጥሮስንና ሌሎቹንም ሐዋርያት፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ታዲያ ምን እናድርግ?” አሏቸው።

38ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም እንዲሰረይላችሁ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።

39የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ እንዲሁም ጌታ አምላካችን ወደ ራሱ ለሚጠራቸው፣ በሩቅ ላሉትም ሁሉ ነውና።”

40በሌላ ብዙ ቃል እየመሰከረላቸው፣ “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ራሳችሁን አድኑ” በማለት አስጠነቀቃቸው።

41ቃሉን የተቀበሉትም ተጠመቁ፤ በዚያ ቀን ሦስት ሺህ ያህል ሰዎች በቍጥራቸው ላይ ተጨመሩ።

42እነርሱም በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት፣ እንጀራውንም በመቍረስና በጸሎት ይተጉ ነበር።

43በሐዋርያት እጅ ብዙ ድንቅና ታምራት ይደረግ ስለ ነበር፣ ሰው ሁሉ ፍርሀት አደረበት።

44ያመኑት ሁሉ በአንድነት ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ የጋራ አደረጉ።

45ሀብታቸውንና ንብረታቸውንም እየሸጡ ለእያንዳንዱ ሰው የሚያስፈልገውን ያህል ይሰጡት ነበር።

46በየዕለቱ በቤተ መቅደስ በአንድነት እየተገናኙ፣ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ በደስታና በቀና ልብ ይመገቡ ነበር፤

47እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው፤ ጌታም የሚድኑትን በቍጥራቸው ላይ ዕለት በዕለት ይጨምር ነበር።

ማብራሪያ

2:1-4

ጌታቸው ከእነርሱ ጋር ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ ማን ይበልጣል በማለት ምን ያህል ጊዜ ይጣሉ እንደነበር ልንረሳው አንችልም፤ አሁን ግን እነዚህ ሁሉ ጠብና ክርክር አልቀዋል። በቅርቡ ደግሞ አብረው ብዙ ጸልየው ነበር። መንፈስ ከላይ በላያችን እንዲፈስልን የምንፈልግ ከሆነ ሁላችንም በአንድ ልብ መሆን አለብን። በነዚያ ደቀ መዛሙርት መካከል እንደነበረው ዓይነት አስተያየቶችና ፍላጎቶች የተለያዩ ቢሆኑም እንኳ፣ እርስ በርስ ለመዋደድ እንስማማ፤ ወንድሞች በአንድነት ቢኖሩ፣ እግዚአብሔር በዚያ በረከቱን ያዝዛልና።

ኃይለኛ ንፋስ በታላቅ ኀይል መጣ። ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ በሰው ልጆች አእምሮ ላይ ያለውን ኃይለኛ ተጽዕኖና ሥራ፣ ከዚያም በዓለም ላይ የሚያደርገውን ነገር ለማመልከት ነበር። እንዲህም የመንፈስ ማሳመኛዎች ለመንፈሱ መጽናናት መንገድ ያዘጋጃሉ፤ የዚያም የተባረከ ንፋስ ኃይለኛ ግፊቶች ነፍስን ለስለስ ላለና ለስላሳ ንፋሱ ያዘጋጃሉ። በዮሐንስ መጥምቅ ስለ ክርስቶስ የተነገረው ቃል እንደሚያሳየው፣ የእሳት ነበልባል የሚመስል ነገር በእያንዳንዳቸው ላይ ሲቀመጥ ታየ፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋልና። መንፈስ እንደ እሳት ልብን ይቀልጣል፣ ጭቃውን ያቃጥላል፣ እናም በነፍስ ውስጥ ሃይማኖታዊና አምላካዊ ስሜቶችን ያነድዳል። በዚህም እንደ መሠዊያው እሳት፣ መንፈሳዊ መሥዋዕቶች ይቀርባሉ።

ከቀድሞው ይልቅ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው ነበር። በመንፈስ ጸጋዎች ተሞልተው ነበር፣ እናም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በመንፈሱ ቅድሳት ተጽዕኖ ሥር ነበሩ፤ ከዚህ ዓለም ይበልጥ ተለይተው ለሌላው ዓለም ይበልጥ ተቀራርበው ነበር። በመንፈስ መጽናናት ይበልጥ ተሞልተው ነበር፣ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በክርስቶስ ፍቅርና በሰማይ ተስፋ ይደሰቱ ነበር፤ በዚህም ሐዘናቸውና ፍርሃታቸው ሁሉ ሙሉ በሙሉ ተዋጠ። በመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ተሞልተው ነበር፤ ወንጌልን ለማስፋፋት ድንቅ ኃይላት ነበራቸው። ቀደም ሲል ከነበረ አስተሳሰብ ወይም ማሰላሰል የተነሳ ሳይሆን፣ መንፈስ እንደሰጣቸው ያህል ተናገሩ።

2:5-13 በባቢሎን የተከሰተው የቋንቋዎች ልዩነት የእውቀትና የሃይማኖት መስፋፋት በከፍተኛ ሁኔታ አግዷል። ጌታ የክርስትናን ሃይማኖት ለማስፋፋት መጀመሪያ የተጠቀመባቸው አገልጋዮች ይህ ስጦታ ባይኖራቸው ኖሮ ምንም እድገት ማድረግ አይችሉም ነበር፤ ይህ ስጦታ ደግሞ ስልጣናቸው ከእግዚአብሔር እንደሆነ አረጋገጠ።

፪፥፲፬-፳፩ የጴጥሮስ ስብከት ከውድቀቱ ሙሉ በሙሉ ማገገሙን፣ እንዲሁም ወደ መለኮታዊው ሞገስ ሙሉ በሙሉ መመለሱን ያሳያልና፤ እርሱ ክርስቶስን የካደው፣ አሁን በድፍረት መስክሮታልና። መንፈስ ቅዱስ በተአምራዊ ሁኔታ ስለፈሰሰበት ሁኔታ የሰጠው ትምህርት አድማጮች የክርስቶስን እምነት እንዲቀበሉ፣ እንዲሁም ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር እንዲቀላቀሉ ታስቦ የተሰጠ ነበር። እርሱም የመጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜ ነበር፤ የክርስቶስም ትንሣኤና ዕርገት ፍሬ፣ ለሁለቱም ማረጋገጫ ነው። ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ የነበረ ቢሆንም፣ መንፈስም በሰጠው መጠን በልሳኖች ቢናገርም፣ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ጎን መተው እንደሌለበት አላሰበም። የክርስቶስ ተማሪዎች ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው በላይ አይማሩም፤ መንፈስም የተሰጠው መጽሐፍ ቅዱስን ለማስቀረት ሳይሆን፣ ነገር ግን እንድንረዳቸው፣ እንድናጸድቃቸውና እንድንታዘዛቸው ለማድረግ ነው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6