1እናንተ ወንድሞች አባቶችም፥ አሁን ለእናንተ ነገሬን ስገልጥ ስሙኝ።
2በዕብራይስጥም ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ ከፊት ይልቅ ዝም አሉ። እርሱም አለ፦
3“እኔ የኪልቅያ በምትሆን በጠርሴስ የተወለድሁ፥ በዚችም ከተማ በገማልያል እግር አጠገብ ያደግሁ፥ የአባቶችንም ሕግ ጠንቅቄ የተማርሁ፥ ዛሬውንም እናንተ ሁሉ እንድትሆኑ ለእግዚአብሔር ቀናተኛ የሆንሁ አይሁዳዊ ሰው ነኝ፡
4ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰርሁ ወደ ወኅኒም አሳልፌ እየሰጠሁ ይህን መንገድ እስከ ሞት ድረስ አሳደድሁ።
5እንዲህም ሊቀ ካህናቱ ደግሞ ሽማግሌዎቹም ሁሉ ይመሰክሩልኛል፤ ከእነርሱ ደግሞ መልእክትን ለወንድሞቻቸው ተቀብዬ፥ በደማስቆ ያሉትን ደግሞ ታስረው እንዲቀጡ ወደ ኢየሩሳሌም ላመጣ ወደዚያ እሄድ ነበር።
6“ስሄድም ወደ ደማስቆ በቀረብሁ ጊዜ፥ ቀትር ሲሆን ድንገት ከሰማይ ታላቅ ብርሃን በዙሪያዬ አንጸባረቀ፤
7በምድርም ላይ ወድቄ፦ ‘ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ?’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ።
8“እኔም መልሼ፦ ‘ጌታ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ?’ አልሁ። እርሱም፦ ‘አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ፡’ አለኝ።
9“ከእኔ ጋር የነበሩትም ብርሃኑን አይተው ፈሩ፥ የሚናገረኝን የእርሱን ድምፅ ግን አልሰሙም።
10‘ጌታ ሆይ፥ ምን ላድርግ?’ አልሁት። ጌታም፦ ‘ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድና ታደርገው ዘንድ ስለ ታዘዘው ሁሉን በዚያ ይነግሩሃል፡’ አለኝ።
11“ከዚያ ብርሃንም ክብር የተነሣ ማየት ባይሆንልኝ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች እጄን ይዘው እየመሩኝ ወደ ደማስቆ ደረስሁ።
12በዚያም የኖሩት አይሁድ ሁሉ የመሰከሩለት እንደ ሕጉም በጸሎት የተጋ ሐናንያ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ።
13እርሱም ወደ እኔ መጥቶ በአጠገቤም ቆሞ፦ ‘ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ እይ፡’ አለኝ። እኔም ያን ጊዜውን ወደ እርሱ አየሁ።
14“እርሱም አለኝ፦ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅ ዘንድና ጻድቁን ታይ ዘንድ ከአፉም ድምፅን ትሰማ ዘንድ አስቀድሞ መርጦሃል።
15ባየኸውና በሰማኸው በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆንለታለህና።
16አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ’።
17“ወደ ኢየሩሳሌምም ከተመለሱ በኋላ በመቅደስ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝ፥
18እርሱም፦ ‘ፍጠን ከኢየሩሳሌምም ቶሎ ውጣ፥ ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና’ ሲለኝ አየሁት።
19“እኔም፦ ‘ጌታ ሆይ፥ በአንተ የሚያምኑትን በምኵራብ ሁሉ እኔ በወኅኒ አገባና እደበድብ እንደ ነበርሁ እነርሱ ያውቃሉ፤
20የሰማዕትህንም የእስጢፋኖስን ደም ባፈሰሱ ጊዜ፥ ራሴ ደግሞ በአጠገባቸው ስቆም ተስማምቼ የገዳዮችን ልብስ እጠብቅ ነበር፡’ አልሁ።
21“እርሱም፦ ‘ሂድ፥ እኔ ወደ አሕዛብ ከዚህ ወደ ሩቅ እልክሃለሁና’ አለኝ።”
22እስከዚህም ቃል ድረስ ይሰሙት ነበር፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው፦ “እንደዚህ ያለውን ሰው ከምድር አስወግደው፥ በሕይወት ይኖር ዘንድ አይገባውምና፡” አሉ።
23ሲጮኹና ልብሳቸውን ሲወረውሩ ትቢያንም ወደ ላይ ሲበትኑ፥
24የሻለቃው ወደ ሰፈሩ እንዲያገቡት አዘዘ፥ እንደዚህም የጮኹበትን ምክንያት ያውቅ ዘንድ፦ “እየገረፋችሁ መርምሩት፡” አላቸው።
25በጠፍርም በገተሩት ጊዜ ጳውሎስ በአጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ፦ “የሮሜን ሰው ያለ ፍርድ ትገርፉ ዘንድ ተፈቅዶላችኋልን?” አለው።
26የመቶ አለቃውም በሰማ ጊዜ ወደ ሻለቃው ቀርቦ፦ “ይህ ሰው ሮማዊ ነውና ታደርገው ዘንድ ካለህ ተጠበቅ፡” ብሎ ነገረው።
27የሻለቃውም ቀርቦ፦ “አንተ ሮማዊ ነህን? ንገረኝ፡” አለው፤ እርሱም፦ “አዎን፡” አለ።
28የሻለቃውም መልሶ፦ “እኔ ይህን ዜግነት በብዙ ገንዘብ አገኘሁት፡” አለ። ጳውሎስም፦ “እኔ ግን በእርስዋ ተወለድሁ፡” አለ።
29ስለዚህም ሊመረምሩት ያሰቡት ከእርሱ ወዲያው ተለዩ፤ የሻለቃውም ደግሞ ሮማዊ መሆኑን ባወቀ ጊዜ ፈራ፥ አሳስሮት ነበርና።
30በማግሥቱም አይሁድ የከሰሱት በምን ምክንያት እንደ ሆነ እርግጡን ያውቅ ዘንድ አስቦ ፈታው፥ የካህናት አለቆችና ሸንጎውም ሁሉ ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ፥ ጳውሎስንም አውርዶ በፊታቸው አቆመው።