የሐዋርያት ሥራ 14

AMHNIVአማርኛ28 ጥቅሶች4:50 አዳምጥ
አዳምጥ 4:50 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በኢቆንዮንም ጳውሎስና በርናባስ አብረው ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ በዚያም በሚገባ ስላስተማሩ፣ ከአይሁድም ከግሪክም እጅግ ብዙ ሰዎች አመኑ።

2ያላመኑት አይሁድ ግን፣ አሕዛብን አነሣሥተው ወንድሞችን እንዲጠሉ አደረጓቸው።

3ጳውሎስና በርናባስም ስለ ጌታ በድፍረት እየተናገሩ ብዙ ጊዜ እዚያው ቈዩ፤ ጌታም የሚናገሩትን የጸጋውን ቃል በታምራዊ ምልክትና በድንቅ ሥራ እየደገፈ ያረጋግጥላቸው ነበር።

4የከተማውም ሕዝብ ተከፋፈለ፤ ገሚሱ ከአይሁድ ጋር፣ ገሚሱም ከሐዋርያት ጋር ሆነ።

5በዚህ ጊዜ አሕዛብና አይሁድ ከመሪዎቻቸው ጋር ተባብረው ሊያንገላቷቸውና በድንጋይ ሊያስወግሯቸው ሞከሩ።

6እነርሱ ግን ይህን እንዳወቁ ልስጥራንና ደርቤን ወደተባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተሞችና በዙሪያቸው ወዳለው አገር ሸሹ፤

7በዚያም ወንጌልን መስበክ ቀጠሉ።

8በልስጥራንም፣ እግሩ አንካሳ የሆነና ከተወለደ ጀምሮ ፈጽሞ በእግሩ ሄዶ የማያውቅ ሽባ ሰው ተቀምጦ ነበር።

9ይህም ሰው ጳውሎስ ሲናገር ያደምጥ ነበር። ጳውሎስም ወደ እርሱ ትኵር ብሎ ተመለከተና ለመዳን እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ

10በታላቅ ድምፅ፣ “ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም!” አለው፤ በዚህ ጊዜ ዘሎ ተነሣና መራመድ ጀመረ።

11ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ፣ በሊቃኦንያ ቋንቋ፣ “አማልክት በሰው ተመስለው ወደ እኛ ወርደዋል!” ብለው ጮኹ፤

12በርናባስን ‘ድያ’ አሉት፤ ጳውሎስም ዋና ተናጋሪ ስለ ነበር ‘ሄርሜን’ አሉት።

13ከከተማው ወጣ ብሎ የነበረው፣ የድያ ቤተ መቅደስ ካህንም ኰርማዎችንና የአበባ ጒንጒኖችን ወደ ከተማው መግቢያ አምጥቶ፣ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው ፈለገ።

14ሐዋርያቱ በርናባስና ጳውሎስ ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል ሮጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤

15“እናንት ሰዎች፤ ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? እኛም እኮ እንደ እናንተው ሰዎች ነን። እናንተም ደግሞ ከዚህ ከንቱ ነገር ርቃችሁ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር እንድትመለሱ ወንጌልን እንሰብክላችኋለን።

16እርሱ ባለፉት ትውልዶች፣ ሕዝቦች ሁሉ በገዛ መንገዳቸው እንዲሄዱ ተዋቸው፤

17ይሁን እንጂ ዝናብን ከሰማይ እንዲሁም ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠቱ፣ ደግሞም ልባችሁን በመብልና በደስታ በማርካቱ መልካምን በማድረግ ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።”

18ይህን ሁሉ ተናግረው እንኳ፣ ሕዝቡ እንዳይሠዋላቸው ያስተዉት በብዙ ችግር ነበር።

19አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጥተው፣ ሕዝቡን አግባቡ፤ ጳውሎስንም በድንጋይ ከወገሩት በኋላ፣ የሞተ መስሎአቸው ጐትተው ከከተማው ወደ ውጭ አወጡት።

20ሆኖም ደቀ መዛሙርት ከበውት እንዳሉ ተነሣ፤ ወደ ከተማም ገባ። በማግስቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ሄዱ።

21ጳውሎስና በርናባስ በደርቤን የምሥራቹን ቃል ሰብከው፣ ብዙ ደቀ መዛሙርትም ካፈሩ በኋላ፣ ወደ ልስጥራን፣ ወደ ኢቆንዮንና ወደ አንጾኪያ ተመለሱ።

22የደቀ መዛሙርቱንም ልብ በማበረታታትና በእምነታቸው ጸንተው እንዲኖሩ በመምከር፣ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ማለፍ አለብን” አሏቸው።

23ከዚያም በየአብያተ ክርስቲያናቱ ሽማግሌዎችን ከሾሙላቸው በኋላ፣ በጾምና በጸሎት ላመኑበት ጌታ ዐደራ ሰጧቸው።

24በጲስድያም ዐልፈው ወደ ጵንፍልያ መጡ፤

25በጴርጌንም ቃሉን ከሰበኩ በኋላ፣ ወደ ኢጣልያ ወረዱ።

26ከአጣልያም፣ እስካሁን ላከናወኑት ሥራ፣ ለእግዚአብሔር ጸጋ በዐደራ ወደ ተሰጡባት ከተማ ወደ አንጾኪያ በመርከብ ተመለሱ።

27እዚያም በደረሱ ጊዜ፣ ቤተ ክርስቲያንን በአንድነት ሰብስበው፣ እግዚአብሔር በእነርሱ አማካይነት ያደረገውን ሁሉ፣ ደግሞም ለአሕዛብ እንዴት የእምነትን በር እንደ ከፈተላቸው ተናገሩ።

28በዚያም ከደቀ መዛሙርት ጋር ብዙ ጊዜ ተቀመጡ።

ማብራሪያ

14:1-7 ሐዋርያት በጣም በግልጽ፣ በመንፈስ ቅዱስ እንደዚህ ባለ ማረጋገጫና ማስረጃ እንዲሁም እንደዚህ ባለ ኃይል፤ በብርቱ ቅንዓትና ለሰዎች ነፍሳት ባላቸው እንደዚህ ያለ ጥልቅ ስጋት ተናገሩ፤ የሰሙአቸውም በእርግጥ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነበር ከማለት በቀር አልቻሉም ነበር። ሆኖም ስኬቱ ለስብከታቸው መንገድ የተሰጠ ሳይሆን ያንን መንገድ ለተጠቀመው ለእግዚአብሔር መንፈስ የተሰጠ ነው። በአደጋዎችና በችግሮች መካከል መልካም በማድረግ መጽናት የጸጋ የተባረከ ማስረጃ ነው። የእግዚአብሔር አገልጋዮች የትም ቢሰደዱ እውነትን ለመናገር መጣር አለባቸው። በክርስቶስ ስምና ኃይል ሲቀጥሉ፣ እርሱም ለጸጋው ቃል ምስክርነት ከመስጠት ወደኋላ አላለም። እርሱ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ አረጋግጦልናል፣ እኛም ነፍሳችንን በእርሱ ላይ ልንታመንበት እንችላለን። አሕዛብና አይሁድ እርስ በእርስ ጠላትነት ነበራቸው፣ ሆኖም ግን በክርስትያኖች ላይ አንድ ሆኑ። የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ለማጥፋት ቢተባበሩ፣ ወዳጆቿስ ለመጠበቅዋ አንድ መሆን የለባቸውምን? እግዚአብሔር ለሕዝቡ በማዕበል ውስጥ መጠጊያ አለው፤ እርሱም መሸሸጊያቸው ነው፣ ይሆናልም። በስደት ዘመን አማኞች የመምህራቸውን ሥራ ባይተዉም እንኳ አንድን ቦታ ለመልቀቅ ምክንያት ሊያገኙ ይችላሉ።

14:8-18 ለሚያምኑ ሁሉ ነገር ይቻላል። እጅግ ውድ የሆነውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እምነት ሲኖረን፣ ከተወለድንበት መንፈሳዊ አቅመ ቢስነት እና ከዚያም ወዲህ ከተፈጠሩት የኃጢአት ልማዶች አገዛዝ ነፃ እንወጣለን፤ በጌታ መንገድ ቀና ብለን ለመቆም እና በደስታ ለመሄድ እንበቃለን። የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ በሰው አምሳል ተገልጦ ብዙ ተአምራትን ባደረገ ጊዜ፣ ሰዎች ለእርሱ መስዋዕት ከማድረግ የራቁ ከመሆናቸው የተነሳ ለትዕቢታቸውና ለክፋታቸው መስዋዕት አደረጉት፤ ጳውሎስና በርናባስ ግን አንድ ተአምር ባደረጉ ጊዜ እንደ አማልክት ተቆጠሩ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6