1የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአሐዝን ወስደው በአባቱ ፈንታ በኢየሩሳሌም አነገሡት።
2ኢዮአሐዝ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ሦስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ወር ገዛ።
3ከዚያም የግብፅ ንጉሥ በኢየሩሳሌም ካለው ዙፋኑ አወረደው፣ በአገሩም ላይ አንድ መቶ መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ግብር ጣለበት።
4የግብፅም ንጉሥ የኢዮአሐዝን ወንድም ኤልያቄምን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው፤ ስሙንም ለውጦ ኢዮአቄም አለው። ኒካዑም የኤልያቄምን ወንድም ኢዮአሐዝን ይዞ ወደ ግብፅ ወሰደው።
5ኢዮአቄም በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ። በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።
6የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በእርሱ ላይ ዘመተ፤ ወደ ባቢሎንም ይወስደው ዘንድ በናስ ሰንሰለት አሰረው።
7እንደዚሁም ናቡከደነፆር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃ ወስዶ፣ ባቢሎን ባለው በራሱ ቤተ ጣዖት አኖረው።
8በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባሩ የፈጸመው አስጸያፊ ድርጊትና በእርሱ ላይ የተገኘበት ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል። ልጁ ዮአኪንም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።
9ዮአኪን በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ወር ከዐሥር ቀን ገዛ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።
10በጸደይም ወራት ንጉሡ ናቡከደነፆር ልኮ በእግዚአብሔ ቤተ መቅደስ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ካላቸው ዕቃዎች ጋር ወደ ባቢሎን ወሰደው። የዮአኪንንም አጎት ሴዴቅያስን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው።
11ሴዴቅያስ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ።
12እርሱም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ የእግዚአብሔርን ቃል በተናገረው በነቢዩ በኤርምያስ ፊትም ራሱን ዝቅ አላደረገም።
13እንደዚሁም በእግዚአብሔር ስም አምሎት በነበረው በንጉሥ ናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ አንገቱን አደነደነ፤ ልቡንም አጠነከረ እንጂ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አልተመለሰም።
14ከዚህም ላይ የካህናቱና የሕዝቡ መሪዎች ሁሉ፣ አስጸያፊ የሆኑትን የአሕዛብን ልማዶች በመከተልና በኢየሩሳሌም የተቀደሰውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በማርከስ፣ ባለ መታመናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሱ ሄዱ።
15የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ፣ መልእክተኞቹን ይልክ ነበር፤
16እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነሣሣና ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ላይ ተሳለቁ፤ ቃሉን ናቁ፤ ነቢያቱንም አቃለሉ።
17ስለዚህ የባቢሎናውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ወጣቶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ፈጀ፤ ወጣቱንም ሆነ ወጣቲቱን፣ ሽማግሌውንም ሆነ በዕድሜ የገፋውን አላስቀረም፤ እግዚአብሔር ሁሉንም ለናቡከደናፆር አሳልፎ ሰጠው።
18እርሱም ትልልቁንም ሆነ ትንንሹን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃ በሙሉ፣ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሀብት፣ የንጉሡንና የሹማምቱን ሀብት ሁሉ ወደ ባቢሎን አጋዘ።
19የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በእሳት አቃጠሉ፤ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች አፈረሱ፤ ቤተ መንግሥቶቹን በሙሉ አቃጠሉ፤ በዚያ የነበረውንም የከበረ ዕቃ በሙሉ አጠፉ።
20ከሰይፍ የተረፉትን ቅሬታዎች በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤ እስከ ፋርስ መንግሥት መነሣትም ድረስ የእርሱና የልጆቹ አገልጋዮች ሆኑ።
21ምድሪቱም የሰንበት ዕረፍት አገኘች፤ በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ ሰባው ዓመት እስኪያበቃ ድረስ፣ ባድማ በነበረችበት ዘመን ሁሉ ዐረፈች።
22በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ዓመት፣ በግዛቱ ሁሉ ዐዋጅ እንዲያስነግርና ይህም እንዲጻፍ እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሣሣ፤ እርሱም እንዲህ አለ፤
23“የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፤ “ ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ በመካከላችሁ የሚገኝ ማናቸውም ሰው፣ እግዚአብሔር አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ እርሱም ወደዚያው ይውጣ።’ ”