1የሳሙኤልም ቃል ወደ እስራኤል ሁሉ ደረሰ። በዚያ ዘመን እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ሊወጉ ወጡ፤ እስራኤላውያን በአቤንኤዘር፣ ፍልስጥኤማውያን ደግሞ በአፌቅ ሰፈሩ።
2ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመግጠም ሰራዊታቸውን አሰለፉ፤ ጦርነቱ እንደ ተፋፋመም፣ እስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን ተሸነፉ፤ በጦርነቱም ላይ አራት ሺህ ያህል እስራኤላውያን ተገደሉ።
3ሰራዊቱ ወደ ሰፈር በተመለሰ ጊዜ የእስራኤል አለቆች፣ ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን እንድንሸነፍ ያደረገን ለምንድን ነው? አብሮን እንዲወጣ፣ ከጠላቶቻችንም እጅ እንዲያድነን የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ከሴሎ እናምጣ” አሉ።
4ስለዚህ ሕዝቡ ሰዎችን ወደ ሴሎ ልከው፣ በኪሩቤል መካከል በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውን የሰራዊት ጌታ የእግዚእብሔርን የኪዳን ታቦት አስመጡ፤ ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ከኪዳኑ ታቦት ጋር በዚያ ነበሩ።
5የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ወደ ሰፈር በገባ ጊዜ፣ ምድሪቱ እስክትናወጥ ድረስ እስራኤላውያን ሁሉ ታላቅ የደስታ ጩኸት አሰሙ።
6ፍልስጥኤማውያንም ይህን ታላቅ ጩኸት ሲሰሙ፣ “በዕብራውያን ሰፈር የምንሰማው ይህ ሁሉ ጩኸት ምንድ ነው?” ሲሉ ጠየቁ። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ ሰፈር መምጣቱን በተረዱ ጊዜ፤
7ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው እንዲህ አሉ፤ “አምላክ ወደ ሰፈሩ መጥቶአል፤ ወዮልን! እንዲህ ዐይነት ነገር ገጥሞን አያውቅም።
8ወዮልን! ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? ግብፃውያንን በምድረ በዳ በልዩ ልዩ መቅሠፍት የመቱ እነዚሁ አማልክት ናቸው፤
9ፍልስጥኤማውያን ሆይ፤ በርቱ ወንድነታችሁም ይታይ፤ ያለዚያ ባሪያ እንዳደረጋችኋቸው ሁሉ፣ ዕብራውያን እናንተን መልሰው ባሪያ ያደርጓችኋል። ወንድነታችሁ ይታይ፤ ተዋጉ!”
10ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ተዋጉ፤ እስራኤላውያንም ስለ ተሸነፉ እያንዳንዱ ወደየድንኳኑ ሸሸ። ታላቅ እልቂት ሆነ፤ ከእስራኤልም ሠላሳ ሺህ እግረኛ ወታደሮች ወደቁ።
11የእግዚአብሔር ታቦት ተማረከ፤ ሁለቱም የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ተገደሉ።
12በዚያች ዕለት አንድ ብንያማዊ ልብሱን ቀዶ፣ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ፣ ከጦሩ ሜዳ እየበረረ ወደ ሴሎ መጣ።
13እዚያ እንደ ደረሰም፣ ዔሊ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ልቡ ስለ ተጨነቀ፣ በመንገድ ዳር ወንበሩ ላይ ተቀምጦ ይጠባበቅ ነበር። ሰውየውም ወደ ከተማው ገብቶ የሆነውን ሁሉ ባወራ ጊዜ፣ ከተማው ሁሉ በጩኸት ተናወጠ።
14ዔሊም ጩኸቱን በሰማ ጊዜ፣ “የምን ጩኸት ነው?” ሲል ጠየቀ። ሰውየውም ፈጥኖ መጣና ለዔሊ ነገረው፤
15ዔሊ የዘጠና ስምንት ዓመት ሽማግሌ ስለ ነበር ዐይኖቹ ደክመው ማየት ተስኖአቸው ነበር።
16ሰውየውም ዔሊን፣ “ከጦሩ ሜዳ ገና አሁን መምጣቴ ነው፤ ከጦርነቱ አምልጬ የወጣሁትም ዛሬውኑ ነው” ብሎ ነገረው። ዔሊም፣ “ልጄ ሆይ፤ ታዲያ እንዴት ሆነ?” ሲል ጠየቀ።
17ወሬውን ያመጣውም ሰው፣ “እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ሰራዊቱም ከፍተኛ እልቂት ደርሶበታል፤ እንዲሁም ሁለቱ ልጆችህ አፍኒንና ፊንሐስ ሞተዋል፤ የእግዚአብሔርም የኪዳኑ ታቦት ተማርኮአል” ብሎ መለሰለት።
18ሰውየው ስለ እግዚአብሔር ታቦት በተናገረ ጊዜ፣ ዔሊ በቅጥሩ በር አጠገብ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ በጀርባው ወደቀ፤ እርሱም ያረጀና ሰውነቱም የሚከብድ ስለ ነበር፣ ዐንገቱ ተሰብሮ ሞተ። እርሱም ለአርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ፈራጅ ነበር።
19በዚያን ጊዜ ምራቱ የፊንሐስ ሚስት፣ ነፍሰ ጡር ነበረች፤ የምትወልድበትም ጊዜ ተቃርቦ ነበር፣ የእግዚአብሔርን ታቦት መማረክ፣ የዐማቷንና የባሏንም መሞት በሰማች ጊዜ ምጡ ስለ ጠናባት ተንበርክካ ወለደች።
20ለመሞትም በምታጣጥርበት ጊዜ፣ በአጠገቧ የነበሩት ሴቶች፣ “አይዞሽ፤ ወንድ ልጅ ወልደሻልና በርቺ” አሏት። እርሷ ግን መልስ አልሰጠችም፤ ልብ ብላም አላዳመጠችም።
21የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከ፣ ዐማቷና ባሏም ስለ ሞቱ፣ “ክብር ከእስራኤል ተለይቶአል” ስትል የሕፃኑን ስም ኢካቦድ አለችው።
22ከዚያም፣ “የእግዚአብሔር ታቦት ተማርኮአልና ክብር ከእስራኤል ተለይቶአል” አለች።