ስምዖን መስቀልን ይሸከማል

19 ቁጥሮች3አማርኛ

ማር 15:21

21አንድ መንገድ አላፊም የአሌክስንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት።

ማር 15:22-36

22ትርጓሜውም የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደተባለ ስፍራ ወሰዱት።

23ከርቤም የተቀላቀለበትን የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም።

24ሰቀሉትም፥ ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ።

25በሰቀሉትም ጊዜ ሦስት ሰዓት ነበረ።

26የክሱ ጽሕፈትም፦ “የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ተጽፎ ነበር።

27ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዶች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ።

28መጽሐፍም፦ “ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ” ያለው ተፈጸመ።

29የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና፦ “ዋ፥ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራ፥

30ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን፡” አሉ።

31እንዲሁም የካህናት አለቆች ደግሞ ከጻፎች ጋር እርስ በርሳቸው እየተዘባበቱ፦ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤

32አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ አሁን ከመስቀል ይውረድ፡” አሉ። ከእርሱም ጋር የተሰቀሉት ይነቅፉት ነበር።

33ስድስት ሰዓትም በሆነ ጊዜ፥ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።

34በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ፦ “ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም፡ “አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው።

35በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው፦ “እነሆ፥ ኤልያስን ይጠራል፡” አሉ።

36አንዱም ሮጦ ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ በመቃም አድርጎ፦ “ተዉ፤ ኤልያስ ሊያወርደው ይመጣ እንደ ሆነ እንይ፡” እያለ አጠጣው።

ማር 15:37-39

37ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ ነፍሱንም ሰጠ።

38የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ።

39በዚያም በአንጻሩ የቆመ የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ፦ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ” አለ።