ማጎትስ
16 ቁጥሮች3አማርኛዘጸ 8:16-19
16እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “አሮንን፦ ‘በትርህን ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ሁሉ ቅማል እንዲሆን የምድሩን ትቢያ ምታ፡’ በለው።”
17እንዲሁም አደረጉ፤ አሮንም እጁን ዘረጋ፥ በበትሩም የምድሩን ትቢያ መታው፥ በሰውና በእንስሳም ላይ ቅማል ሆነ፤ በግብፅ አገር ሁሉ የምድር ትቢያ ሁሉ ቅማል ሆነ።
18ጠንቋዮችም በአስማታቸው ያወጡ ዘንድ እንዲሁ አደረጉ፥ ነገር ግን አልቻሉም፤ ቅማሉም በሰውና በእንስሳ ላይ ነበረ።
19ጠንቋዮችም ፈርዖንን፦ “ይህስ የእግዚአብሔር ጣት ነው፡” አሉት፤ የፈርዖን ልብ ግን ጸና፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ አልሰማቸውም።
ዘጸ 8:20-24
20እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “ማልደህ ተነሣ፥ በፈርዖንም ፊት ቁም፤ እነሆ እርሱ ወደ ውኃ ይወርዳል፤ እንዲህም በለው፦ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ።
21ሕዝቤንም ባትለቅቅ፥ እነሆ በአንተ በባሪያዎችህም በሕዝብህም በቤቶችህም ላይ የዝንብ መንጎች እሰድዳለሁ፤ የግብፃውያን ቤቶች የሚኖሩባትም ምድር ሁሉ በዝንብ መንጎች ይሞላሉ።
22በዚያን ቀን በምድር መካከል እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቅ ዘንድ፥ በዚያ የዝንብ መንጋ እንዳይሆን ሕዝቤ የሚቀመጥባትን የጌሤምን ምድር እለያለሁ።
23በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል እለያለሁ፤ ይህም ተአምራት ነገ ይሆናል።’ ”
24እግዚአብሔርም እንዲሁ አደረገ፤ በፈርዖንም ቤት በባሪያዎቹም ቤቶች ውስጥ ብዙ የዝንብ መንጋ መጣ፤ በግብፅም አገር ሁሉ ላይ ከዝንቡ መንጋ የተነሣ ምድር ጠፋች።
ዘጸ 9:1-7
1እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “ወደ ፈርዖን ዘንድ ገብተህ ንገረው፦ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።
2ልትለቅቃቸውም እንቢ ብትል፡ ብትይዛቸውም፥
3እነሆ የእግዚአብሔር እጅ በሜዳ ውስጥ ባሉት በከብቶችህ፥ በፈረሶችም በአህዮችም በግመሎችም በበሬዎችም በበጎችም ላይ ትሆናለች፤ ብርቱ ቸነፈርም ይወርዳል።
4እግዚአብሔርም በእስራኤልና በግብፅ ከብቶች መካከል ይለያል፤ ከእስራኤልም ልጆች ከብት አንዳች አይጠፋም።’ ”
5እግዚአብሔርም፦ “ነገ እግዚአብሔር ይህን ነገር በምድር ላይ ያደርጋል፡” ብሎ ጊዜን ወሰነ።
6እግዚአብሔርም ያንን ነገር በነጋው አደረገ፥ የግብፅም ከብት ሁሉ ሞተ፤ ከእስራኤል ልጆች ከብት ግን አንድ ስንኳ አልሞተም።
7ፈርዖንም ላከ፥ እነሆም ከእስራኤል ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አልሞተም። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም።