ማርያም ኤልሳቤጥን ጎበኘች።
25 ቁጥሮች3አማርኛሉቃ 1:39-45
39ማርያምም በዚያ ወራት ተነሥታ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ከተማ ፈጥና ወጣች፥
40ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ኤልሳቤጥን ተሳለመቻት።
41ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥
42በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው።
43የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?
44እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና።
45ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት።”
ሉቃ 1:46-53
46ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥
47መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤
48የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤
49“ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው።
50ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል።
51“በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤
52ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤
53የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል።
ሉቃ 1:57-66
57የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፥ ወንድ ልጅም ወለደች።
58ጎረቤቶችዋም ዘመዶችዋም ጌታ ምሕረቱን እንዳገነነላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ደስ አላቸው።
59በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፥ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ወደዱ።
60እናቱ ግን መልሳ፦ “አይሆንም፥ ዮሐንስ ይባል እንጂ” አለች።
61እነርሱም፦ “ከወገንሽ ማንም በዚህ ስም የተጠራ የለም” አሉአት።
62አባቱንም ማን ሊባል እንዲወድ ጠቀሱት።
63ብራናም ለምኖ፦ “ስሙ ዮሐንስ ነው፡” ብሎ ጻፈ። ሁሉም አደነቁ።
64ያንጊዜም አፉ ተከፈተ መላሱም ተፈታ እግዚአብሔርንም እየባረከ ተናገረ።
65ለጎረቤቶቻቸውም ሁሉ ፍርሃት ሆነ፤ ይህም ሁሉ ነገር በይሁዳ በተራራማው አገር ሁሉ ተወራ፤
66የሰሙትም ሁሉ፦ “እንኪያ ይህ ሕፃን ምን ይሆን?” እያሉ በልባቸው አኖሩት፤ የጌታ እጅ ከእርሱ ጋር ነበረችና።