ከሞት በኋላ ያለው ሕይወት

32 ቁጥሮችአማርኛ

1ኛ ቆሮ 15:1-32

1ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤

2በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ።

3እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን፡ ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ፦ “መጽሐፍ እንደሚል፡ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥

4ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል፡ በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥

5ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤

6ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤

7ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤

8ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ።”

9እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፤

10ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም።

11እንግዲህስ እኔ ብሆን እነርሱም ቢሆኑ እንዲሁ እንሰብካለን እንዲሁም አመናችሁ።

12ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን፡ ከእናንተ አንዳንዶቹ፦ “ትንሣኤ ሙታን የለም፥” እንዴት ይላሉ?

13ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤

14ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤

15ደግሞም፦ “ክርስቶስን አስነሥቶታል፤” ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም።

16ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣማ፤

17ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ።

18እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ።

19በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።

20አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል።

21ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና።

22ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።

23ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው፤

24በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል።

25ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና።

26የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤

27ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን፦ “ሁሉ ተገዝቶአል፡” ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው።

28ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።

29እንዲያማ ካልሆነ፥ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው?

30እኛስ ዘወትር በሚያስፈራ ኑሮ የምንኖር ስለ ምንድር ነው?

31በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለኝ በእናንተ ትምክህት እየማልሁ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕለት ዕለት እሞታለሁ።

32እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ።