ኢየሱስ የኢያኢሮስን ልጅ አስነሣ
17 ቁጥሮችአማርኛሉቃ 8:40-56
40ኢየሱስም በተመለሰ ጊዜ ሁሉ ይጠብቁት ነበርና ሕዝቡ ተቀበሉት።
41እነሆም፥ ኢያኢሮስ የሚባል ሰው መጣ፥ እርሱም የምኵራብ አለቃ ነበረ በኢየሱስም እግር ላይ ወድቆ ወደ ቤቱ እንዲገባ ለመነው፤
42አሥራ ሁለት ዓመት የሆናት አንዲት ሴት ልጅ ነበረችውና፤ እርስዋም ለሞት ቀርባ ነበረች። ሲሄድም ሕዝቡ ያጨናንቁት ነበር።
43ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ ትዳርዋንም ሁሉ ለባለመድኃኒቶች ከስራ ማንም ሊፈውሳት አልተቻለውም።
44በኋላውም ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፥ የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ።
45ኢየሱስም፦ “የዳሰሰኝ ማን ነው?” አለ። ሁሉም በካዱ ጊዜ፥ ጴጥሮስና ከእርሱ ጋር የነበሩት፦ “አቤቱ፥ ሕዝቡ ያጫንቁሃልና ያጋፉህማል፤ ‘የዳሰሰኝ ማን ነው’ ትላለህን?” አሉ።
46ኢየሱስ ግን፦ “አንድ ሰው ዳስሶኛል፥ ኃይል ከእኔ እንደ ወጣ እኔ አውቃለሁና” አለ።
47ሴቲቱም እንዳልተሰወረች ባየች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፥ በምን ምክንያትም እንደ ዳሰሰችው ፈጥናም እንደ ተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት አወራች።
48እርሱም፦ “ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” አላት።
49እርሱም ገና ሲናገር አንድ ሰው ከምኵራብ አለቃው ቤት መጥቶ፦ “ልጅህ ሞታለች፤ እንግዲህ መምህሩን አታድክም” አለ።
50ኢየሱስ ግን ሰምቶ፦ “አትፍራ፤ እመን ብቻ ትድንማለች” ብሎ መለሰለት።
51ወደ ቤትም ሲገባ ከጴጥሮስና ከያዕቆብ ከዮሐንስም ከብላቴናይቱም አባትና እናት በቀር ማንም ከእርሱ ጋር ይገባ ዘንድ አልፈቀደም።
52ሁሉም እያለቀሱላት ዋይ ዋይ ይሉ ነበር። እርሱ ግን፦ “አታልቅሱ፤ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አለ።
53እንደ ሞተችም አውቀው በጣም ሳቁበት።
54እርሱ ግን እጅዋን ይዞ፦ “አንቺ ብላቴና፥ ተነሺ፡” ብሎ ጮኸ።
55ነፍስዋም ተመለሰች፥ ፈጥናም ቆመች፥ የምትበላውንም እንዲሰጡአት አዘዘ።
56ወላጆችዋም ተገረሙ፤ እርሱ ግን የሆነውን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው።