ትንቢተ ዘካርያስ 8

AMHNIVአማርኛ23 ጥቅሶች4:32 አዳምጥ
አዳምጥ 4:32 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እንደ ገናም የእግዚአብሔር ጸባኦት ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “ስለ ጽዮን እጅግ ቀንቻለሁ፤ ስለ እርሷም በቅናት ነድጃለሁ።

3እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ወደ ጽዮን እመለሳለሁ፤ በኢየሩሳሌም እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌምም የእውነት ከተማ ትባላለች፤ የእግዚአብሔር ጸባኦት ተራራም ቅዱስ ተራራ ይባላል።”

4እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “ሽማግሌዎችና አሮጊቶች እንደ ገና በኢየሩሳሌም አደባባይ ይቀመጣሉ፤ እያንዳንዳቸውም ከዕድሜአቸው ብዛት የተነሣ ምርኵዝ ይይዛሉ።

5የከተማዪቱም አደባባዮች እዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ።”

6እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “በዚያን ጊዜ ይህ ለቀረው የእስራኤል ሕዝብ አስደናቂ መስሎ ሊታይ ይችላል፤ ለእኔ ግን አስደናቂ ሊሆን ይችላልን?” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

7እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቤን ከምሥራቅና ከምዕራብ አገር እታደጋለሁ።

8በኢየሩሳሌም እንዲኖሩ መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም በጽድቅና በታማኝነት አምላካቸው እሆናለሁ።”

9እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “የእግዚአብሔር ጸባኦት ቤት መሠረት ሲጣል፣ በዚያ የነበሩ ነቢያት የተናገሩትን ቃል አሁን የምትሰሙ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመሥራት እጃችሁን አበርቱ።

10ከዚያ በፊት ለሰው ደመወዝ፣ ለእንስሳም ኪራይ አይከፈልም ነበር፤ ጠላት በመኖሩም ማንም ሥራውን በሰላም ማከናወን አልቻለም፤ እያንዳንዱ ሰው በባልንጀራው ላይ እንዲነሣ አድርጌ ነበርና።

11አሁን ግን ቀድሞ እንዳደረግሁት በዚህ በቀረው ሕዝብ ላይ አላደርግም” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

12“ዘሩ ጥሩ ሆኖ ይበቅላል፤ ወይኑ ፍሬውን ያፈራል፤ ምድሪቱ አዝመራዋን ታበረክታለች፤ ሰማያትም ጠላቸውን ይሰጣሉ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ለቀሪው ሕዝብ ርስት አድርጌ እሰጣለሁ።

13የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፤ በአሕዛብ መካከል የርግማን ምሳሌ ነበራችሁ፤ አሁን ግን አድናችኋለሁ፤ እናንተም በረከት ትሆናላችሁ። አትፍሩ፤ ነገር ግን እጃችሁን አበርቱ።”

14እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “አባቶቻችሁ ባስቈጡኝ ጊዜ ያላንዳች ሐዘኔታ ጥፋት ላመጣባችሁ እንደ ወሰንሁ፣” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት፤

15“አሁን ደግሞ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ መልካም ነገርን ላደርግ ወስኛለሁ፤ አትፍሩ።

16ልታደርጓቸው የሚገባችሁ ነገሮች እነዚህ ናቸው፤ እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ፤ በአደባባያችሁም እውነትንና ትክክለኛ ፍርድን አስፍኑ፤

17በባልንጀራችሁ ላይ ክፋትን በልባችሁ አታውጠንጥኑ፤ በሐሰት መማልን አትውደዱ፤ እነዚህን ሁሉ እጸየፋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።

18እንደ ገናም የእግዚአብሔር ጸባኦት ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

19እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “የአራተኛው፣ የአምስተኛው፣ የሰባተኛውና የዐሥረኛው ወር ጾሞች ለይሁዳ ቤት የደስታ፣ የተድላና የሐሤት በዓላት ይሆናሉ፤ ስለዚህ እውነትንና ሰላምን ውደዱ።”

20እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “ብዙ ሕዝቦችና የብዙ ከተሞች ነዋሪዎች ገና ይመጣሉ፤

21የአንዲቱ ከተማ ነዋሪዎችም፣ ‘እግዚአብሔርን ለመለመን እግዚአብሔር ጸባኦትን ለመፈለግ፣ ኑ፤ በፍጥነት እንሂድ፤ እኔም ራሴ እሄዳለሁ’ እያሉ ወደ ሌላዪቱ ከተማ ይሄዳሉ።

22ብዙ ሕዝብና ኀያላን መንግሥታትም እግዚአብሔር ጸባኦትን ለመፈለግና ለመለመን ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ።”

23እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “በእነዚያም ቀናት ከየወገኑና ከየቋንቋው ዐሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ አጥብቀው በመያዝ፣ “ ‘እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ’ ” ይሉታል።

ማብራሪያ

8:1-8 የጽዮን ኃጢአቶች ትልልቅ ጠላቶቿ ነበሩ። እግዚአብሔር ኃጢአቶቿን ያስወግዳል፤ ከዚያም ሌላ ጠላት አይጎዳትም። ሃይማኖት የመሰከሩ ሰዎች ሃይማኖታቸውን በአምልኮተ እግዚአብሔርና በቅንነት ማስዋብ አለባቸው። እውነት የሰፈነባት ከተማና የቅድስና ተራራ በምትሆንበት ጊዜ፣ ኢየሩሳሌም ሰላማዊና ብልጽግና ያላት ትሆናለች።

ቁጥር 4 እና 5፣ ከብዛት፣ ከልከኝነትና ከእርካታ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ታላቅ ውጫዊ ሰላም ውብ በሆነ መንገድ ይገልጻሉ። የተበተኑት እስራኤላውያን ከሁሉም አቅጣጫዎች ይሰበሰባሉ። እግዚአብሔር በርህራሄው ፈጽሞ አይተዋቸውም ወይም አይጥላቸውም፤ ይህን የገባላቸው ቃል ነውና፤ እነርሱም በግዴታ መንገድ እርሱን ፈጽሞ አይተዉትም ወይም አይጥሉትም፣ እርሱንም ቃል እንደገቡለት። እነዚህ ተስፋዎች በከፊል የተፈጸሙት በአይሁድ ቤተክርስቲያን ውስጥ፣ ከምርኮ በኋላ እስከ ክርስቶስ መምጣት ዘመን ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፤ በወንጌል ቤተክርስቲያንም ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተፈጽመዋል፤ ነገር ግን ሙሉ ትርጉማቸው የወደፊቱን የክርስቲያን ቤተክርስቲያን ዘመናት ወይም የአይሁድን ወደፊት መመለስን የሚያመለክት መሆን አለበት።

በሰው ዘንድ ይህ የማይቻል ነው፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ነገር ይቻላል፤ የእግዚአብሔር ሀሳቦችና መንገዶች ከእኛ እጅግ የላቁ ናቸውና። አሁን ባለው የሕያው አምልኮተ እግዚአብሔር ዝቅተኛ ሁኔታ፣ እንዲህ ያለ ሙሉ ለውጥ ሊደረግ ይችላል ብለን ማሰብ ይከብደናል፤ ነገር ግን እንዲህ ያለ ሰፊና የከበረ ለውጥ በአዲስ ፈጣሪው መንፈስ ሁሉን በሚችል ኃይል ሊከናወን ይችላል፣ ዓለምን ለመፍጠር ከፈጀበት ጊዜ ባነሰ ጊዜ ውስጥ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6