1አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ከአንቺ ጋር እንፈልገው ዘንድ ውድሽ ወዴት ሄደ? ውድሽስ ወዴት ፈቀቅ አለ?
2ውዴ በገነቱ መንጋውን ያሰማራ ዘንድ፡ አበባውንም ይሰበስብ ዘንድ፡ ወደ ሽቱ መደብ ወደ ገነቱ ወረደ።
3እኔ የወዴ ነኝ ውዴም የእኔ ነው፤ በሱፉ አበባ መካከል መንጋውን ያሰማራል።
4ወዳጄ ሆይ፥ እንደ ቴርሳ ውብ ነሽ፥ እንደ ኢየሩሳሌምም ያማርሽ ነሽ፤ ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት ታስፈሪያለሽ።
5አውከውኛልና ዓይኖችሽን ከፊቴ መልሺ፤ ጠጕርሽ ከገለዓድ እንደ ወረደ እንደ ፍየል መንጋ ነው።
6ጥርሶችሽ ታጥበው እንደ ወጡ፡ ሁሉ መንታ እንደ ወለዱ፡ ከእነርሱም መካን እንደሌለባቸው መንጎች ናቸው።
7በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ጕንጭና ጕንጭሽ፡ እንደ ተከፈለ ሮማን ናቸው።
8ስድሳ ንግሥታት ሰማንያም ቍባቶች፡ ቍጥር የሌላቸውም ቈነጃጅት አሉ።
9ርግቤ መደምደሚያዬም አንዲት ናት፤ ለእናትዋ አንዲት ናት ለወለደቻትም የተመረጠች ናት። ቈነጃጅትም አይተው አሞገሱአት፥ ንግሥታትና ቍባቶችም አመሰገኑአት።
10ይህች እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጐበኝ፥ እንደ ጨረቃ የተዋበች እንደ ፀሐይም የጠራች፥ ዓላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ማን ናት?
11የወንዙን ዳር ልምላሜ አይ ዘንድ፥ ወይኑ አብቦ ሮማኑም አፍርቶ እንደ ሆነ እመለከት ዘንድ፡ ወደ ገውዝ ገነት ወረድሁ።
12ሳላውቅ ነፍሴ በከበረው ሰረገላ ላይ አስቀመጠችኝ።
13አንቺ ሱላማጢስ ሆይ፥ ተመለሽ፥ ተመለሽ እናይሽ ዘንድ ተመለሽ፥ ተመለሽ። በሱላማጢስ ምን ታያላችሁ? እርስዋ እንደ መሃናይም ዘፈን ናት።