ወደ ሮሜ 10

AMHNIVአማርኛ21 ጥቅሶች3:06 አዳምጥ
አዳምጥ 3:06 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ወንድሞች ሆይ፤ ስለ እስራኤላውያን የልቤ ምኞት፣ እግዚአብሔርንም የምለምነው እንዲድኑ ነው።

2ለእግዚአብሔር ቀናተኞች እንደሆኑ ስለ እነርሱ መመስከር እችላለሁና፤ ቅናታቸው ግን ከዕውቀት የተነሣ አይደለም።

3ከእግዚአብሔር የሚመጣውን ጽድቅ ስላላወቁና የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት ስለ ፈለጉ፣ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም።

4ለሚያምን ሁሉ ጽድቅ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና።

5ሙሴ በሕግ በኩል የሆነውን ጽድቅ ሲገልጽ፣ “እነዚህን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ ይኖራል” ይላል።

6ከእምነት የሆነው ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፤ “ ‘በልብህ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል?’ አትበል”፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤

7“ወይም ‘ወደ ጥልቁስ ማን ይወርዳል?’ አትበል”፤ ይህም ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው።

8ነገር ግን ምን ይላል? “ቃሉ በአጠገብህ ነው፤ በአፍህና በልብህም ውስጥ ነው፤” የምንሰብከውም የእምነት ቃል ይህ ነው፤

9“ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ።

10የምትጸድቀው በልብህ አምነህ ነው፤ የምትድነውም በአፍህ መስክረህ ነውና።

11መጽሐፍ እንደሚለው፣ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም።”

12በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ልዩነት የለም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፤ የሚለምኑትንም አብዝቶ ይባርካል፤

13“የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።”

14ታዲያ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ስለ እርሱስ ሳይሰሙ እንዴት ያምኑበታል? ሰባኪ ሳይኖር እንዴት መስማት ይችላሉ?

15ካልተላኩስ እንዴት መስበክ ይችላሉ? ይህም፣ “የምሥራችን የሚያመጡ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው!” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

16ነገር ግን የሰሙት ሁሉ የምሥራቹን ቃል አልተቀበሉም፤ ኢሳይያስም፣ “ጌታ ሆይ፤ መልእክታችንን ማን አምኖአል?” ብሎአልና።

17እንግዲያስ እምነት የሚገኘው መልእክቱን ከመስማት ነው፤ መልእክቱም በክርስቶስ ቃል ነው።

18ነገር ግን አልሰሙ ይሆን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በርግጥ ሰምተዋል፤ “ድምፃቸው በምድር ሁሉ፣ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ተሰማ።”

19ደግሜም እጠይቃለሁ፤ እስራኤል አላስተዋሉ ይሆን? በቅድሚያ ሙሴ እንዲህ ይላል፤ “ሕዝብ ባልሆኑት አስቀናቸዋለሁ፤ ማስተዋል በሌለው ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ”

20ኢሳይያስም በድፍረት፣ “ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፤ ላልጠየቁኝ ራሴን ገለጥሁላቸው” ይላል።

21ስለ እስራኤል ግን፣ “ወደማይታዘዝና እሺ ወደማይል ሕዝብ፣ ቀኑን ሙሉ እጄን ዘረጋሁ” ይላል።

ማብራሪያ

ሮሜ 10:1-4 አይሁድ በሐሰት መሠረት ላይ ተመሰረቱ፣ በእምነት ወደ ክርስቶስ በመምጣትም ነፃውን ድነት ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም። በየዘመናቱም ብዙዎች በተለያየ መንገድ እንዲሁ ያደርጋሉ። የሕጉ ጥብቅነት ለሰዎች በጸጋ በእምነት የሚያገኙት ድነት እንደሚያስፈልጋቸው አሳያቸው። የአምልኮ ሥርዓቶቹም ክርስቶስ ጽድቅን እንደሚፈጽምላቸውና የሕጉን መርገም እንደሚሸከምላቸው በጥላ አመለከቱ። ስለዚህም ከሕግ በታችም እንኳ በእግዚአብሔር ዘንድ ጽድቅ የተሰጣቸው ሁሉ ያንን በረከት በእምነት አገኙ፤ በዚህም በተስፋ የተደረገለት የቤዛው ፍጹም ጽድቅ ተካፋዮች ሆኑ። ሕጉ አልተሻረም፣ የሕግ ሰጪውም ዓላማ አልከሸፈም፤ ነገር ግን ሕጉን በመተላለፋችን ምክንያት በክርስቶስ ሞት ሙሉ ካሳ ስለተገኘ፣ ዓላማው ተሳክቷል። ማለትም፣ ክርስቶስ ሕጉን በሙሉ ፈጽሟልና፤ ስለዚህም በእርሱ የሚያምን ማንኛውም ሰው፣ እርሱ ራሱ ሕጉን በሙሉ እንደፈጸመ ያህል፣ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ እንደሆነ ይቆጠራል። ኃጢአተኞች እግዚአብሔርን እንደ ገዥ ያለውን ፍትህ፣ ወይም እንደ አዳኝ ያለውን ጽድቅ ቢያውቁ ኖሮ፣ የራሳቸውን ጽድቅ በከንቱ አስተሳሰብ መቀጠል ፈጽሞ አይችሉም ነበር።

10:5-11 ራሱን የኮነ ኃጢአተኛ ይህ ጽድቅ እንዴት ሊገኝ እንደሚችል ራሱን ማወክ አያስፈልገውም። ክርስቶስን ስለማየት፣ ስለመቀበልና በእርሱ ስለመመገብ ስንናገር፣ የምንለው በሰማይ ያለውን ክርስቶስን ወይም በጥልቁ ያለውን ክርስቶስን አይደለም፤ ነገር ግን በተስፋ ቃል ውስጥ ያለውን ክርስቶስን፣ በቃሉ የተገለጠውን ክርስቶስን ነው። በክርስቶስ በማመን የሚገኘው ጽድቅ ግልጽ ትምህርት ነው። ለሁሉም ሰው አእምሮና ልብ የቀረበ ነው፤ ይህም ላለመታመን ምንም ምክንያት አይተውለትም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6