1እግዚአብሔር ሆይ፤ በቍጣህ አትገሥጸኝ፤ በመዓትህም አትቅጣኝ።
2እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐቅመ ቢስ ነኝና ማረኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐጥንቶቼ ተናግተዋልና ፈውሰኝ።
3ነፍሴ እጅግ ታውካለች፤ እስከ መቼ፤ አንተ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ እስከ መቼ ድረስ ይሆናል?
4እግዚአብሔር ሆይ፤ ተመለስና ሕይወቴን ታደጋት፤ ስለ ጽኑ ፍቅርህም አድነኝ፤
5በሞት የሚያስታውስህ የለምና፤ በሲኦልስ ማን ያመሰግንሃል?
6ከመቃተቴ የተነሣ ዝያለሁ፤ ሌሊቱን ሁሉ በልቅሶ ዐልጋዬን አርሳለሁ፤ መኝታዬንም በእንባዬ አሾቃለሁ።
7ዐይኖቼ በሐዘን ብዛት ደክመዋል፤ ከጠላቶቼም ሁሉ የተነሣ ማየት ተስኖአቸዋል።
8እናንተ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ፤ ከእኔ ራቁ፤ እግዚአብሔር የልቅሶዬን ድምፅ ሰምቶአልና።
9እግዚአብሔር ልመናዬን አድምጦአል፤ እግዚአብሔር ጸሎቴን ይቀበላል።
10ጠላቶቼ ሁሉ ያፍራሉ፤ እጅግም ይደነግጣሉ፤ በመጡበት ይመለሳሉ፤ ድንገትም ይዋረዳሉ።