1የጽድቄ አምላክ ሆይ፤ በጠራሁህ ጊዜ መልስልኝ፤ ከጭንቀቴ አሳርፈኝ፤ ማረኝ፤ ጸሎቴንም ስማ።
2ሰዎች ሆይ፤ እስከ መቼ ድረስ ክብሬን ዝቅ ታደርጋላችሁ? እስከ መቼስ ድረስ ከንቱ ነገርን ትወዳላችሁ? ሐሰትንስ ትሻላችሁ? ሴላ
3እግዚአብሔር ጻድቁን ለራሱ እንደ ለየ ዕወቁ፤ እግዚአብሔር ወደ እርሱ በተጣራሁ ጊዜ ይሰማኛል።
4ስትቈጡ ኀጢአት አትሥሩ፤ በዐልጋችሁም ላይ ሳላችሁ፣ ልባችሁን መርምሩ፤ ጸጥም በሉ። ሴላ
5የጽድቅን መሥዋዕት አቅርቡ፤ በእግዚአብሔርም ታመኑ።
6ብዙዎች፣ “አንዳች በጎ ነገር ማን ያሳየናል?” ይላሉ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የፊትህ ብርሃን በላያችን ይብራ።
7ስንዴና አዲስ የወይን ጠጅ በብዛት ባመረቱ ጊዜ ከሚያገኙት ደስታ ይልቅ፣ አንተ ልቤን በታላቅ ሐሤት ሞልተኸዋል።
8በሰላም እተኛለሁ፤ አንቀላፋለሁም፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ያለ ሥጋት የምታሳድረኝ አንተ ብቻ ነህና።