1ሕዝቦች ሁላችሁ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፤ ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር እልል በሉ።
2በምድር ሁሉ ላይ ታላቅ የሆነው ንጉሥ፣ ልዑል እግዚአብሔር የሚያስፈራ ነውና።
3ሕዝቦችን ከእኛ በታች አደረገ፤ መንግሥታትንም ከእግራችን ሥር አስገዛልን።
4ለሚወደው ለያዕቆብ ክብር የሆነችውን፣ ርስታችንን እርሱ መረጠልን። ሴላ
5አምላክ በእልልታ፣ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።
6አምላካችንን አወድሱት፤ አወድሱት፤ ንጉሣችንን አወድሱት፤ አወድሱት፤
7እግዚአብሔር የምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና፤ ምርጥ ዝማሬ አቅርቡለት።
8እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ ነግሦአል፤ እግዚአብሔር በተቀደሰ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦአል።
9ከአብርሃም አምላክ ሕዝብ ጋር፣ የሕዝቦች መኳንንት ተሰበሰቡ፤ የምድር ነገሥታት የእግዚአብሔር ናቸውና፤ እርሱም እጅግ ከፍ ከፍ ያለ ነው።