1አምላክ ሆይ፤ መጠጊያዬ ነህና፣ በከለላህ ሰውረኝ።
2እግዚአብሔርን፣ ‘አንተ ጌታዬ ነህ፤ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም” አልሁት።
3በምድር ያሉ ቅዱሳን፣ ሙሉ ደስታ የማገኝባቸው ክቡራን ናቸው።
4ሌሎችን አማልክት የሚከተሉ፣ ሐዘናቸው ይበዛል፤ እኔ ግን የደም ቍርባናቸውን አላፈስም፤ ስማቸውንም በአፌ አልጠራም፤
5እግዚአብሔር የርስት ድርሻዬና ጽዋዬ ነው፤ ዕጣዬም በእጅህ ናት።
6መካለያ ገመድ ባማረ ስፍራ ተጥሎልኛል፤ በርግጥም የተዋበች ርስት አግኝቻለሁ።
7የሚመክረኝን እግዚአብሔርን እባርካለሁ፤ በሌሊት እንኳ ልቤ ቀናውን ያመላክተኛል።
8እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አድርጌአለሁ፤ እርሱ በቀኜ ስላለ አልናወጥም።
9ስለዚህ ልቤ ደስ አለው፤ ነፍሴም ሐሤት አደረገች፤ ሥጋዬም ያለ ሥጋት ዐርፎ ይቀመጣል፤
10በሲኦል ውስጥ አትተወኝምና፤ ቅዱስህም መበስበስን እንዲያይ አታደርግም።
11የሕይወትን መንገድ ታሳየኛለህ፤ በአንተ ዘንድ የደስታ ሙላት፣ በቀኝህም የዘላለም ፍሥሓ አለ።