1አቤቱ፥ ዳዊትን ገርነቱንም ሁሉ አስብ፤
2ለእግዚአብሔር እንደ ማለ፥ ለያዕቆብም አምላክ እንደ ተሳለ፦
3“በእውነት ወደ ቤቴ ድንኳን አልገባም፥ ወደ ምንጣፌም አልጋ አልወጣም፥
4ለዓይኖቼም መኝታ ለሽፋሽፍቶቼም እንቅልፍ፥ ለጕንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም፥
5ለእግዚአብሔር ስፍራ፥ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ድረስ” ብሎ።
6እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር ውስጥም አገኘነው።
7ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን።
8አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት።
9ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ፥ ቅዱሳንህም ደስ ይበላቸው።
10ስለ ዳዊት ስለ ባሪያህ፡ የቀባኸውን ሰው ፊት አትመልስ።
11እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ አይጸጸትምም፥ እንዲህ ብሎ፦ “ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ።
12ልጆችህ ኪዳኔን፥ ይህንም የማስተምራቸውን ምስክሬን ቢጠብቁ፥ ልጆቻቸው ደግሞ በዙፋንህ ላይ ለዘላለም ይቀመጣሉ።”
13እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ፦
14“ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ።
15አሮጊቶችዋን እጅግ እባርካለሁ፥ ድሆችዋንም እንጀራ አጠግባለሁ።
16ካህናቶችዋንም ደኅንነትን አለብሳቸዋለሁ፥ ቅዱሳኖችዋም እጅግ ደስ ይላቸዋል።
17በዚያ ለዳዊት ቀንድን አበቅላለሁ፥ ለቀባሁትም ሰው መብራትን አዘጋጃለሁ።
18ጠላቶችንም እፍረትን አለብሳቸዋለሁ፤ በእርሱ ግን ቅድስናዬ ያብባል።”