1ልጄ ሆይ፤ ለጎረቤትህ ዋስ ብትሆን፣ ስለ ሌላውም ሰው እጅ መትተህ ቃል ብትገባ፣
2በተናገርኸው ነገር ብትጠመድ፣ ከአፍህ በወጣውም ቃል ብትያዝ፣
3ልጄ ሆይ፤ ራስህን ለማዳን ይህን አድርግ፤ በጎረቤትህ እጅ ስለ ወደቅህ፣ ሄደህ ራስህን አዋርድ፤ ጎረቤትህን አጥብቀህ ነዝንዘው።
4ዐይኖችህ እንቅልፍ አይያዛቸው፣ ሽፋሽፍቶችህም አያንጐላጁ።
5ከአዳኝ እጅ እንዳመለጠች ሚዳቋ፣ ከአጥማጅ ወጥመድ እንዳፈተለከች ወፍ ራስህን አድን።
6አንተ ታካች፤ ወደ ጒንዳን ሂድ፤ ዘዴውን አስተውለህ ጠቢብ ሁን፤
7አዛዥ የለውም፤ አለቃም ሆነ ገዥ የለውም፤
8ሆኖም ግን በበጋ ምግቡን ያከማቻል፤ በመከርም ወቅት ቀለቡን ይሰበስባል።
9አንተ ታካች፤ እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ?
10ጥቂት ማንቀላፋት፤ ጥቂት ማንጐላቸት፤ እጅን አጣጥፎ “እስቲ ጥቂት ልረፍ” ማለት፤
11ድኽነት እንደ ወንበዴ፣ ዕጦትም መሣሪያ እንደ ታጠቀ ሰው ከተፍ ይልብሃል።
12ወሮበላና ጨካኝ፣ ነውረኛ አንደበቱን ይዞ የሚዞር፣
13በዐይኑ የሚጠቅስ፣ በእግሩ ምልክት የሚሰጥ፣ በጣቶቹ የሚጠቊም፣
14በልቡ ተንኰል ክፋትን የሚያውጠነጥን፣ ምንጊዜም ጠብ ይጭራል።
15ስለዚህ በቅጽበት መዓት ይወርድበታል፤ በድንገት ይጠፋል፤ መዳኛም የለውም።
16እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፤ የሚጸየፋቸውም ሰባት ናቸው፤ እነርሱም፦
17ትዕቢተኛ ዐይን፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆች፣
18ክፋትን የሚያውጠነጥን ልብ፣ ወደ ክፋት የሚቻኰሉ እግሮች፣
19በውሸት ላይ ውሸት የሚጨምር ሐሰተኛ ምስክር፣ በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚጭር ሰው።
20ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ትእዛዝ አክብር፤ የእናትህንም ትምህርት አትተው።
21ምንጊዜም በልብህ አኑራቸው፤ በዐንገትህም ዙሪያ እሰራቸው።
22በምትሄድበት ሁሉ ይመሩሃል፤ በምትተኛበት ጊዜ ይጠብቁሃል፤ በምትነቃበት ጊዜም ያነጋግሩሃል።
23እነዚህ ትእዛዞች መብራት ናቸውና፤ ይህችም ትምህርት ብርሃን፣ የተግሣጽ ዕርምትም የሕይወት መንገድ ናት፤
24እርሷም ከምግባረ ብልሹ ሴት፣ ልዝብ አንደበት ካላት ዘልዛላ ሴት ትጠብቅሃለች።
25ውበቷን በልብህ አትመኝ፤ በዐይኗም አትጠመድ፤
26ጋለሞታ ሴት ቊራሽ እንጀራ ታሳጣሃለችና፤ አመንዝራዪቱም በሕይወትህ በራሱ ላይ ትሸምቃለች።
27ለመሆኑ ልብሱ ሳይቃጠል፣ በጒያው እሳት መያዝ የሚችል ሰው አለን?
28አንድ ሰው እግሮቹ ሳይቃጠሉ፣ በፍም ላይ መሄድ ይችላልን?
29ከሰው ሚስት ጋር የሚተኛም እንደዚሁ ነው፤ የሚደርስባትም ከቅጣት አያመልጥም።
30ሌባ በተራበ ጊዜ ራቡን ለማስታገሥ ቢሰርቅ፣ ሰዎች አይንቁትም።
31በቤቱ ያለውን ሀብት ሁሉ የሚጠይቀው ቢሆንም፣ ከተያዘ ሰባት ዕጥፍ መክፈል አለበት።
32የሚያመነዝር ሰው ግን ማመዛዘን ይጐድለዋል፤ እንዲህ የሚያደርግ ሁሉ ራሱን ያጠፋል።
33መደብደብና ውርደት ዕጣው ነው፤ ኀፍረቱም ከቶ አይወገድም፤
34ቅናት የባልን ቊጣ ይቀሰቅሳልና፤ በሚበቀልበትም ጊዜ ምሕረት አያደርግም።
35ምንም ዐይነት ካሣ አይቀበልም፤ የቱንም ያህል ብዙ ቢሆን መማለጃን እሺ አይልም።