ትንቢተ ናሆም 1

AMHEVGአማርኛ15 ጥቅሶች2:44 አዳምጥ
አዳምጥ 2:44 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ስለ ነነዌ የተነገረ ሸክም፤ የኤልቆሻዊው የናሆም የራእዩ መጽሐፍ ይህ ነው።

2እግዚአብሔር ቀናተኛና ተበቃይ አምላክ ነው፤ እግዚአብሔር ተበቃይና መዓትን የተሞላ ነው፤ እግዚአብሔር ተቃዋሚዎቹን ይበቀላል፥ ለጠላቶቹም ቍጣውን ይጠብቃል።

3እግዚአብሔር ትዕግሥተኛ፥ ኃይሉም ታላቅ ነው፥ በደለኛውንም፦ “ንጹሕ ነህ፡” አይልም፤ እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።

4ባሕሩንም ይገሥጻታል፥ ያደርቃትማል፥ ወንዞችንም ሁሉ ያደርቃል፤ ባሳንና ቀርሜሎስም ላልተዋል፥ የሊባኖስም አበባ ጠውልጎአል።

5ተራሮችም ከእርሱ የተነሣ ታወኩ፥ ኮረብቶችም ቀለጡ፤ ምድርና ዓለም የሚኖሩበትም ሁሉ ከፊቱ ተናወጡ።

6በቍጣው ፊት የሚቆም ማን ነው? የቍጣውንም ትኵሳት ማን ይታገሣል? መዓቱ እንደ እሳት ይፈስሳል፥ ከእርሱም የተነሣ ዓለቶች ተሰነጠቁ።

7እግዚአብሔር መልካም ነው፥ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል።

8ስፍራዋን ግን በሚያጥለቀልቅ ጎርፍ ፈጽሞ ያጠፋታል፥ ጠላቶቹንም ወደ ጨለማ ያሳድዳቸዋል።

9በእግዚአብሔር ላይ የምታስቡት ምንድር ነው? እርሱ ፈጽሞ ያጠፋል፥ መከራም ሁለተኛ አይነሣም።

10እርስ በእርሳቸው እንደ ተመሰቃቅለ እሾህ ቢሆኑ፥ በመጠጣቸውም ቢሰክሩ እንደ ደረቅ ገለባ ፈጽመው ይጠፋሉ።

11በእግዚአብሔር ላይ በክፉ የሚያስብ፥ ክፋትን የሚመክር፥ ከአንተ ዘንድ ወጥቶአል።

12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ኃይለኞችና ብዙዎች ቢሆኑ እንዲሁ ይቈረጣሉ፥ እርሱም ያልቃል። እኔም አስጨንቄሃለሁ፥ ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ አላስጨንቅህም።

13አሁንም ቀንበሩን ከአንተ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ።”

14እግዚአብሔርም ከስምህ ማንም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይዘራ ስለ አንተ አዝዞአል፤ ከአምላኮችህ ቤት የተቀረጸውንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል አጠፋለሁ፤ አንተም የተጠቃህ ነህና መቃብርህን እምሳለሁ።

15እነሆ፥ የምስራችን የሚያመጣ ሰላምንም የሚያወራ ሰው እግር በተራሮች ላይ ነው! ይሁዳ ሆይ፥ አጥፊው ፈጽሞ ጠፍቶአልና፥ ከእንግዲህም ወዲህ በአንተ ዘንድ አያልፍምና ዓመት በዓሎችህን አድርግ፥ ስእለቶችህን ክፈል።

ማብራሪያ

1:1-8 ከመቶ ዓመት ገደማ በፊት በዮናስ ስብከት የነነዌ ሰዎች ንስሐ ገብተው ከጥፋት ቢድኑም፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ከበፊቱ ይበልጥ ክፉዎች ሆኑ። ነነዌ ከእርሷ ጋር የሚከራከረውን አምላክ አታውቅም፤ እርሱ ግን ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ተነገራት። ስለ እርሱ እዚህ ከተነገረው ጋር እምነትን መቀላቀል ለሁሉም መልካም ነው፤ ይህ ለክፉዎች ታላቅ ፍርሃትን፣ ለምእመናን ደግሞ መጽናናትን ይናገራል። እያንዳንዱ ሰው የራሱን ድርሻ ከእርሱ ይውሰድ፦ ኃጢአተኞች ያንብቡትና ይንቀጥቀጡ፤ ቅዱሳንም ያንብቡትና ይደሰቱ። የጌታ ቁጣ ለሕዝቡ ካለው በጎነት ጋር ተነጻጽሯል። ምናልባት እነርሱ በዓለም ዘንድ የማይታወቁና ከቁም ነገር የማይቆጠሩ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ነገር ግን ጌታ ያውቃቸዋል። በቅዱስ መጽሐፍ የተገለጸው የይሖዋ ባሕርይ ከትዕቢተኞች አሳብ ጋር አይስማማም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6