ትንቢተ ናሆም 1

AMHNIVአማርኛ15 ጥቅሶች2:49 አዳምጥ
አዳምጥ 2:49 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ስለ ነነዌ ጥፋት የተነገረ ንግር፤ የኤልቆሻዊው የናሆም የራእዩ መጽሐፍ ይህ ነው፤

2እግዚአብሔር ቀናተኛና ተበቃይ አምላክ ነው፤ እግዚአብሔር የሚበቀል፣ በመዓትም የተሞላ ነው። እግዚአብሔር ባላጋራዎቹን ይበቀላል፤ በጠላቶቹም ላይ ቍጣውን ያመጣል

3እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ በኀይሉም ታላቅ ነው፤ እግዚአብሔር በደለኛውን ሳይቀጣ አያልፍም፤ መንገዱ በዐውሎ ነፋስና በማዕበል ውስጥ ነው፤ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።

4ባሕርን ይገሥጻል፤ ያደርቀዋልም፤ ወንዞችን ሁሉ ያደርቃል። ባሳንና ቀርሜሎስ ጠውልገዋል፤ የሊባኖስም አበቦች ረግፈዋል።

5ተራሮች በፊቱ ታወኩ፤ ኰረብቶችም ቀለጡ። ምድር በፊቱ፣ ዓለምና በውስጧ የሚኖሩት ሁሉ ተናወጡ።

6ቊጣውን ማን ሊቋቋም ይችላል? ጽኑ ቊጣውንስ ማን ሊሸከም ይችላል? መዓቱ እንደ እሳት ፈሶአል፤ ዐለቶችም በፊቱ ተሰነጣጥቀዋል።

7እግዚአብሔር መልካም ነው፤ በጭንቅ ጊዜም መሸሸጊያ ነው። ለሚታመኑበት ይጠነቀቅላቸዋል፤

8ነነዌን ግን፣ በሚያጥለቀልቅ ጐርፍ ያጠፋታል፤ ጠላቶቹንም ወደ ጨለማ ያሳድዳቸዋል።

9በእግዚአብሔር ላይ ምንም ቢያሤሩ፣ እርሱ ያጠፋዋል፤ መከራም ዳግመኛ አይነሣም።

10በእሾህ ይጠላለፋሉ፤ በወይን ጠጃቸውም ይሰክራሉ፤ እሳትም እንደ ገለባ ይበላቸዋል።

11ነነዌ ሆይ፤ በእግዚአብሔር ላይ የሚያሤር፣ ክፋትንም የሚመክር፣ ከአንቺ ዘንድ ወጥቶአል።

12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ምንም ኀይለኞችና ብዙዎች ቢሆኑም፣ ይቈረጣሉ፤ ይጠፋሉም። ይሁዳ ሆይ፤ ከዚህ በፊት ባስጨንቅህም፣ ከእንግዲህ አላስጨንቅህም።

13አሁንም ቀንበራቸውን ከዐንገትህ ላይ አንሥቼ እሰብራለሁ፤ የታሰርህበትንም ሰንሰለት በጥሼ እጥላለሁ።”

14አንቺ ነነዌ፤ እግዚአብሔር ስለ አንቺ እንዲህ ብሎ አዞአል፤ “ስም የሚያስጠራ ትውልድ አይኖራችሁም፤ በአማልክቶቻችሁ ቤት ያሉትን፣ የተቀረጹትን ምስሎችና ቀልጠው የተሠሩትን ጣዖታት እደመስሳለሁ፤ መቀበሪያህን እምስልሃለሁ፤ አንተ ክፉ ነህና።

15እነሆ፤ የምሥራች የሚያመጣው፣ ሰላምን የሚያውጀው ሰው እግር፣ በተራሮች ላይ ነው፤ ይሁዳ ሆይ፤ በዓላትህን አክብር፤ ስእለትህንም ፈጽም፤ ከእንግዲህ ክፉዎች አይወሩህም፤ እነርሱም ፈጽመው ይጠፋሉ።

ማብራሪያ

1:1-8 ከመቶ ዓመት ገደማ በፊት በዮናስ ስብከት የነነዌ ሰዎች ንስሐ ገብተው ከጥፋት ቢድኑም፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ከበፊቱ ይበልጥ ክፉዎች ሆኑ። ነነዌ ከእርሷ ጋር የሚከራከረውን አምላክ አታውቅም፤ እርሱ ግን ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ተነገራት። ስለ እርሱ እዚህ ከተነገረው ጋር እምነትን መቀላቀል ለሁሉም መልካም ነው፤ ይህ ለክፉዎች ታላቅ ፍርሃትን፣ ለምእመናን ደግሞ መጽናናትን ይናገራል። እያንዳንዱ ሰው የራሱን ድርሻ ከእርሱ ይውሰድ፦ ኃጢአተኞች ያንብቡትና ይንቀጥቀጡ፤ ቅዱሳንም ያንብቡትና ይደሰቱ። የጌታ ቁጣ ለሕዝቡ ካለው በጎነት ጋር ተነጻጽሯል። ምናልባት እነርሱ በዓለም ዘንድ የማይታወቁና ከቁም ነገር የማይቆጠሩ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ነገር ግን ጌታ ያውቃቸዋል። በቅዱስ መጽሐፍ የተገለጸው የይሖዋ ባሕርይ ከትዕቢተኞች አሳብ ጋር አይስማማም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6