የማርቆስ ወንጌል 3

AMHNIVአማርኛ35 ጥቅሶች4:57 አዳምጥ
አዳምጥ 4:57 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በሌላ ጊዜ ወደ ምኵራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር።

2በምክንያት ሊከሱት የሚፈልጉ ሰዎችም በሰንበት ቀን ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት ይጠባበቁ ነበር።

3እርሱም እጁ የሰለለችውን ሰው፣ “በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ተነሥተህ ቁም” አለው።

4ኢየሱስም፣ “በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነው ወይስ ክፉ? ሕይወት ማዳን ነውን ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። እነርሱ ግን ዝም አሉ።

5በልባቸው ደንዳናነት አዝኖ በዙሪያው የቆሙትን በቍጣ ተመለከታቸውና ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ!” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እጁም ፍጹም ደኅና ሆነችለት።

6ፈሪሳውያንም እንዴት ሊያጠፉት እንደሚችሉ ከሄሮድስ ወገን ከሆኑት ጋር መመካከር ጀመሩ።

7ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባሕሩ ሄደ፤ ከገሊላ የመጣ እጅግ ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤

8የሚሠራውን ነገር የሰሙ ሰዎችም ከይሁዳ፣ ከኢየሩሳሌም፣ ከኤዶምያስ፣ በዮርዳኖስ ማዶ ካለው አገር እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢ ወደ እርሱ መጡ።

9የተሰበሰበውም ሕዝብ እንዳያጨናንቀው አነስተኛ የሆነ ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው።

10ብዙዎችን ፈውሶ ስለ ነበር፣ በሕመም የሚሠቃዩ ሁሉ ሊዳስሱት ይሽቀዳደሙ ነበር።

11ርኩሳን መናፍስትም ባዩት ቍጥር ከፊቱ እየወደቁ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” በማለት ይጮኹ ነበር።

12እርሱ ግን ማንነቱን እንዳይገልጹ አጥብቆ ይገሥጻቸው ነበር።

13ኢየሱስ ወደ ተራራ ወጥቶ የሚፈልጋቸውን ወደ እርሱ እንዲመጡ ጠራቸው፤ እነርሱም ወደ እርሱ መጡ።

14ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ፣ ለስብከትም ይልካቸው ዘንድ ዐሥራ ሁለቱን ሾማቸው፤ ሐዋርያትም ብሎ ጠራቸው፤

15አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው።

16የሾማቸውም ዐሥራ ሁለቱ እነዚህ ናቸው፤ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖን፣

17ቦአኔርጌስ ይኸውም፣ “የነጐድጓድ ልጆች” ብሎ የጠራቸው የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፤

18እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ በርቶሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ታዴዎስ፣ ተቀናቃኙ ስምዖን፣

19እንዲሁም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ።

20ከዚያም ኢየሱስ ወደ አንድ ቤት ገባ፤ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ምግብ መብላት እንኳ እስኪሳናቸው ድረስ ሕዝቡ እንደ ገና በብዛት ተሰበሰበ።

21ሁኔታውን የሰሙ ዘመዶቹም፣ “አእምሮውን ስቶአል” በማለት ይዘውት ለመሄድ ወዳለበት መጡ።

22ከኢየሩሳሌም የመጡ ጸሐፍትም፣ “ብዔልዜቡል አድሮበታል፤ አጋንንትን የሚያወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” አሉ።

23እርሱም ጠራቸውና በምሳሌ እንዲህ አላቸው፤ “ሰይጣን ሰይጣንን እንዴት ሊያስወጣ ይችላል?

24እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሊጸና አይችልም፤

25ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ሊቆም አይችልም።

26እንደዚሁም ሰይጣን እርስ በርሱ የሚፃረርና የሚከፋፈል ከሆነ ሊቆም አይችልም፤ ያበቃለታል።

27ከዚህም የተነሣ አንድ ሰው አስቀድሞ ኀይለኛውን ሰው ሳያስር ወደ ኀይለኛው ሰው ቤት ሊገባና ንብረቱን ሊዘርፍ አይችልም፤ ቤቱን መዝረፍ የሚቻለው ኀይለኛውን ሰው ሲያስር ብቻ ነው።

28እውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጆች ኀጢአትና የሚሳደቡት ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤

29ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ የዘላለም ኀጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም።”

30ይህንንም ያለው፣ “ርኩስ መንፈስ አለበት” ስላሉት ነበር።

31ከዚህ በኋላ እናቱና ወንድሞቹ መጡ፤ በውጭ ቆመውም ሰው ልከውበት አስጠሩት።

32በዙሪያው የተቀመጡ ብዙ ሰዎችም፣ “እነሆ፤ እናትህና ወንድሞችህ ውጭ ይፈልጉሃል” አሉት።

33እርሱም መልሶ፣ “እናቴ ማን ናት ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አላቸው።

34በዙሪያው ወደ ተቀመጡትም በመመልከት፣ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው!

35የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ወንድሜ፣ እኅቴ፣ እናቴም ነውና።”

ማብራሪያ

3:1-5 የዚህ ሰው ጉዳይ እጅግ የሚያሳዝን ነበር፤ የደረቀች እጅ ነበረችውና ከኑሮው እንዳይሠራ ያደርገው ነበር፤ እንዲህ ያሉ ደግሞ ለምጽዋት እጅግ ተገቢ ናቸው። ራሳቸውን መርዳት የማይችሉ ይረዱ ዘንድ ይገባል። ነገር ግን ግትር የሆኑ የማያምኑ ሰዎች በእውነት ላይ ሊናገሩት የሚችሉት ነገር ባይኖራቸውም እንኳ አይታዘዙም። እኛ የተሳሳተውን ንግግር እንሰማለን፣ የተሳሳተውንም ሥራ እናያለን፤ ክርስቶስ ግን በልብ ውስጥ ያለውን የመራራነት ሥር፣ የዚያን ዕውርነትና ደንዳናነት ይመለከታል፣ ያዝናልም። ደንዳና ልብ ያላቸው ኃጢአተኞች የቁጣው ቀን ሲደርስ በቅርቡ በሚመለከታቸው ቁጣ እንዴት እንደሚመለከታቸው ሲያስቡ ይንቀጥቀጡ። አሁን ታላቁ የመፈወስ ቀን ሰንበት ነው፣ የመፈወሻ ቦታ ደግሞ የጸሎት ቤት ነው፤ ነገር ግን የመፈወስ ኃይል የክርስቶስ ነው። የወንጌል ትእዛዝ በዚህ እንደ ተመዘገበው ነው፤ እጆቻችን የደረቁ ቢሆኑም፣ ባንዘረጋቸው ግን፣ ያልተፈወስንበት ምክንያት የእኛ ጥፋት ነው። ነገር ግን ከተፈወስን፣ ክርስቶስ፣ ኃይሉና ጸጋው የከበረውን ሁሉ ሊያገኝ ይገባል።

3:6-12

ሁሉም ደዌዎቻችንና መከራዎቻችን በኃጢአቶቻችን ላይ ከሚነደው የእግዚአብሔር ቁጣ የሚመነጩ ናቸው። መወገዳቸውና በረከት እንዲሆኑልን መደረጉም በክርስቶስ ደም ተገዝቶልናል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6