የማርቆስ ወንጌል 10

AMHNIVአማርኛ52 ጥቅሶች8:08 አዳምጥ
አዳምጥ 8:08 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ይሁዳ አገርና በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው አካባቢ ሄደ፤ ሕዝቡም እንደ ገና በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ከዚህ ቀደም ያደርገው እንደ ነበረውም አስተማራቸው።

2አንዳንድ ፈሪሳውያንም መጥተው፣ “ሰው ሚስቱን መፍታት ይገባዋልን?” ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት።

3እርሱም መልሶ፣ “ሙሴ ምን ብሎ አዘዛችሁ?” አላቸው።

4እነርሱም፣ “ሙሴማ የፍች ወረቀት ጽፎ እንዲፈታት ፈቅዶአል” አሉ።

5ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ ይህን ሕግ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንዳና በመሆኑ ነው።

6ነገር ግን በፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።

7ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፤

8ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤

9ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ማንም አይለየው።”

10እንደ ገና ወደ ቤት በገቡ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱ ይህንኑ አንሥተው ጠየቁት።

11እርሱም፣ “ማንም ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ በእርሷ ላይ ያመነዝራል፤

12እርሷም ባሏን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች” አላቸው።

13ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው፣ ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው።

14ኢየሱስም ይህን ሲያይ ተቈጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና።

15እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።”

16ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው።

17ከዚያ ተነሥቶ መንገዱን ሲጀመር፣ አንድ ሰው ወደ እርሱ እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጒልበቱ ተንበርክኮ፣ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል” አለው።

18ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ቸር የለም፤

19ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አታታልል፤ አባትህንና እናትህን አክብር።”

20ሰውየውም፣ “መምህር ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ጠብቄአለሁ” አለው።

21ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ “እንግዲያው አንድ ነገር ይጐድልሃል፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሽጥ፤ ለድኾችም ስጥ፤ በሰማይ የተከማቸ ሀብት ታገኛለህ፤ ከዚያ በኋላ ና፤ ተከተለኝም” አለው።

22ሰውየው ይህን ሲሰማ ክፉኛ አዘነ፤ ብዙ ሀብት ስለ ነበረውም እየተከዘ ሄደ።

23ኢየሱስ ዙሪያውን በመመልከት ደቀ መዛሙርቱን፣ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው!” አላቸው።

24ደቀ መዛሙርቱም በንግግሩ ተገረሙ፤ ኢየሱስ ግን እንደ ገና መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ልጆች ሆይ፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው!

25ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀለዋል።”

26ደቀ መዛሙርቱም ይበልጥ በመገረም፣ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ።

27ኢየሱስም አያቸውና፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል” አላቸው።

28ጴጥሮስም፣ “እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ” አለው።

29ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም እኅቶቹን ወይም እናቱን ወይም አባቱን ወይም ልጆቹን ወይም ዕርሻውን የተወ ሁሉ፣

30አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና ዕርሻን መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይወርስ የለም።

31ነገር ግን ብዙ ፊተኞች የሆኑ ኋለኞች፣ ኋለኞች የሆኑም ፊተኞች ይሆናሉ።”

32ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት በመንገድ ላይ ሳሉ፣ ኢየሱስ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ተገረሙ፣ ሌሎች የተከተሉት ደግሞ ፈርተው ነበር። ደግሞም ዐሥራ ሁለቱን ከሕዝቡ ለይቶ ምን እንደሚደርስበት ነገራቸው፤

33እንዲህም አላቸው፤ “ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ አሳልፈው ለአሕዛብ ይሰጡታል፤

34ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፣ ይገርፉታል፣ ከዚያም ይገድሉታል፤ እርሱ ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።”

35ከዚያም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “መምህር ሆይ፤ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንፈልጋለን” አሉት።

36እርሱም፣ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።

37እነርሱም፣ “በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝህ፣ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” አሉት።

38ኢየሱስም፣ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፣ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?” አላቸው።

39እነርሱም፣ “አዎን እንችላለን” አሉት። ኢየሱስም፣ “እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤

40ነገር ግን በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ ለተዘጋጀላቸው የሚሆን እንጂ እኔ የምሰጠው ነገር አይደለም” አላቸው።

41ዐሥሩ ይህን ሲሰሙ፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን መቈጣት ጀመሩ።

42ኢየሱስም በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ አለቆች ተብለው የሚታሰቡት እንደሚገዟቸው፤ ሹሞቻቸውም በእነርሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ ታውቃላችሁ፤

43በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋይ ይሁን፤

44ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤

45የሰው ልጅ ሊያገለግልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሊገለገል አልመጣምና።”

46ከዚህ በኋላ ወደ ኢያሪኮ መጡ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጡ ዐይነ ስውሩ የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር።

47እርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን በሰማ ጊዜ፣ “የዳዊት ልጅ፣ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ ይጮኽ ጀመር።

48ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ የባሰ ጮኸ።

49ኢየሱስም ቆም ብሎ፣ “ጥሩት” አላቸው። እነርሱም ዐይነ ስውሩን፣ “አይዞህ፤ ተነሥ፤ ይጠራሃል!” አሉት።

50እርሱም ልብሱን ጥሎ ብድግ በማለት፣ ተነሥቶ ወደ ኢየሱስ መጣ።

51ኢየሱስም፣ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” አለው። ዐይነ ስውሩም፣ “መምህር ሆይ፤ እንዳይ እፈልጋለሁ” አለው።

52ኢየሱስም፣ “ሂድ፣ እምነትህ አድኖሃል” አለው፤ ወዲያውም ዐይኑ በራለት፤ በመንገድም ኢየሱስን ተከትሎት ሄደ።

ማብራሪያ

10:1-12

ኢየሱስ በነበረበት ሁሉ ሕዝቡ በብዛት ወደ እርሱ ይጎርፍ ነበር፤ እርሱም ያስተምራቸው ነበር። መስበክ የክርስቶስ የማያቋርጥ ተግባር ነበር። እርሱም በዚህ ስፍራ የሚያሳየው፣ የሙሴ ሕግ ፍቺን የፈቀደበት ምክንያት እነርሱ ያንን ፈቃድ ሊጠቀሙበት የማይገባ እንደሆነና ይህ የሆነውም የልባቸው እልህ የተነሳ ብቻ መሆኑን ነው። እግዚአብሔር ራሱ ወንድና ሴትን አጣምሯልና፤ እርስ በእርስ መጽናኛና እርዳታ እንዲሆኑም ፈጥሯቸዋል። እግዚአብሔር ያሰረውን ማኅበር በቀላሉ ሊፈታ አይገባም። ሚስቶቻቸውን የሚፈቱ ሁሉ እግዚአብሔር በተመሳሳይ መንገድ ቢያደርግባቸው በራሳቸው ላይ ምን ሊደርስ እንደሚችል ያስቡ።

10:13-16 አንዳንድ ወላጆች ወይም ሞግዚቶች ትንንሽ ልጆችን ወደ ክርስቶስ አመጡ፤ እርሱም እንዲነካቸው፣ እንደ በረከቱም ምልክት እንዲሆንላቸው ነበር። የአካል ፈውስ እንደሚያስፈልጋቸው አይመስልም ነበር፤ ሊማሩም የሚችሉ አልነበሩም። ነገር ግን እነርሱን ይንከባከቡ የነበሩት የክርስቶስ በረከት ለነፍሳቸው መልካም እንደሚያደርግላቸው ያምኑ ነበር፤ ስለዚህም ወደ እርሱ አመጧቸው። ኢየሱስም ወደ እርሱ እንዲያመጧቸው አዘዘ፤ ምንም ነገርም እንዳይከለክላቸው እንዳይነገርም ሆነ እንዳይደረግ ተናገረ። ልጆች ቃሉን መረዳት እንደቻሉ ወዲያውኑ ወደ አዳኝ ሊመሩ ይገባል። በተጨማሪም የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ትንንሽ ልጆች ልንቀበል ይገባናል። ለክርስቶስና ለጸጋው ያለን አመለካከት ደግሞ እንደ ትንንሽ ልጆች ለወላጆቻቸው፣ ለሞግዚቶቻቸውና ለመምህሮቻቸው ሊሆን ይገባል።

10:17-22 ይህ ወጣት ባለሥልጣን ታላቅ ትጋት አሳይቷል። አሁን ምን ማድረግ እንዳለበት፣ ለዘላለም ደስታ እንዲያገኝ ብሎ ጠየቀ። አብዛኞቹ በዚህ ዓለም ሊገኝ የሚችለውን መልካም ነገር ይጠይቃሉ፤ ማንኛውንም መልካም ነገር፣ መዝ 4:6፤ እርሱ ግን በዚህ ዓለም ሊሠራ የሚገባውን መልካም ነገር ጠየቀ፣ በሌላው ዓለም ታላቁን መልካም ነገር ለመጎናጸፍ ሲል። ክርስቶስም እምነቱን በመርዳትና አኗኗሩን በመምራት ይህን ጥያቄውን አበረታታው። ነገር ግን በኢየሱስና በዚህ ወጣት መካከል የሚያሳዝን መለያየት ተፈጠረ። የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት፣ እስካሁን ከሠራው በላይ ምን ማድረግ እንዳለበት ክርስቶስን ጠየቀ፤ ክርስቶስም የዘላለም ሕይወትን በተመለከተ እንዳለው ከሚመስለው፣ በእርግጥም ያ ጽኑ እምነትና ከፍተኛ ግምት ያለው ስለመሆኑ ጠየቀው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6