ትንቢተ ሚክያስ 6

AMHNIVአማርኛ16 ጥቅሶች3:11 አዳምጥ
አዳምጥ 3:11 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እግዚአብሔር የሚለውን ስሙ፤ “ተነሡ፤ ጒዳያችሁን በተራሮችም፤ ፊት አቅርቡ፤ ኰረብቶች እናንተ የምትሉትን ይስሙ፤

2ተራሮች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ክስ አድምጡ፤ እናንት የምድር ጽኑ መሠረቶችም፤ ስሙ፤ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ክርክር አለውና፤ ከእስራኤልም ጋር ይፋረዳል።

3“ሕዝቤ ሆይ፤ ምን አድርጌሃለሁ? ሸክም የሆንሁብህስ እንዴት ነው? እስቲ መልስልኝ!

4ከግብፅ አወጣሁህ፤ ከባርነት ምድርም ተቤዠሁህ፤ እንዲመሩህ ሙሴን፣ አሮንንና ማርያምን ላክሁልህ።

5ሕዝቤ ሆይ፤ የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ የመከረውን፣ የቢዖር ልጅ በለዓም የመለሰለትንም እስቲ አስቡ፤ የእግዚአብሔርን የጽድቅ ሥራ ታውቁ ዘንድ፣ ከሰጢም እስከ ጌልገላ የተጓዛችሁትን አስቡ።

6ምን ይዤ በእግዚአብሔር ፊት ልቅረብ፣ በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ ከአንድ ዓመት ጥጃ ጋር ይዤ በፊቱ ልቅረብን?

7በአንድ ሺህ አውራ በጎች፣ በዐሥር ሺህ የዘይት ፈሳሽ እግዚአብሔር ደስ ይለዋልን? ስለ በደሌ የበኵር ልጄን፣ ስለ ነፍሴም ኀጢአት የሆዴን ፍሬ ላቅርብለትን?

8ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?

9ስምህን መፍራት ጥበብ ነው፤ ስሙ! እግዚአብሔር ከተማዪቱን እንዲህ እያለ ይጣራል፤ “በትሩን አስቡ፤ ያዘጋጀውም ማን እንደሆነ አስታውሱ።

10የክፋት ቤት ሆይ፤ በግፍ የተገኘ ሀብታችሁን፣ በሐሰተኛ መስፈሪያ የሰበሰባችሁትን አስጸያፊ ነገር እረሳዋለሁን?

11አባይ ሚዛን የያዘውን ሰው፣ ሐሰተኛ መመዘኛ በከረጢት የቋጠረውን ንጹሕ ላድርገውን?

12ባለጠጎቿ ግፈኞች፣ ሰዎችዋ ሐሰተኞች ናቸው፤ ምላሳቸውም አታላይ ናት።

13ስለዚህ አንተን አጠፋሃለሁ፣ ከኀጢአትህ የተነሣ አፈራርስሃለሁ።

14ትበላለህ፤ ነገር ግን አትጠግብም፤ ሆድህ እንዳለ ባዶውን ይቀራል፤ ታከማቻለህ፤ ነገር ግን አይጠራቀምልህም፤ የሰበሰብኸውን ለሰይፍ አደርገዋለሁና።

15ትዘራለህ፤ ነገር ግን አታጭድም፤ የወይራ ዘይት ትጨምቃለህ፤ ነገር ግን ዘይቱን አትቀባም፤ ወይንን ትቈርጣለህ፤ ነገር ግን የወይን ጠጅ አትጠጣም።

16የዖምሪን ሥርዐት፣ የአክዓብን ቤት ልምድ ሁሉ የሙጥኝ ብለሃል፤ ትውፊታቸውንም ተከትለሃል። ስለዚህ አንተን ለውድመት፣ ሕዝብህን ለመዘባበቻ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ አሕዛብም ይሣለቁብሃል።”

ማብራሪያ

6:1-5 ሕዝቡ የእግዚአብሔርን አምልኮ ለምን እንደሰለቻቸውና ወደ ጣዖት አምልኮም ለምን እንዳደሉ እንዲገልጹ ይጠየቃሉ። ኃጢአት በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ለሚፈጠረው ክርክር መንስኤ ይሆናል። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚከራከረው ራሳችንን እንድንመረምር ለማስተማር ነው። እነርሱም እግዚአብሔር ለእነርሱና ለአባቶቻቸው ያደረጋቸውን ብዙ ቸርነቶች ያስታውሱ፤ ከዚያም እነርሱ ለእርሱ ያሳዩትን የማይገባና ምስጋና የጎደለውን ምግባር ከእነዚያ ቸርነቶች ጋር ያወዳድሩ።

ሚክያስ 6:6-8

እነዚህ ጥቅሶች በለዓቅ የእስራኤልን አምላክ ሞገስ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ከበለዓም ጋር ያደረገው ምክክር ዋና ይዘት የያዙ ይመስላሉ። የጥፋተኝነትና የቁጣ ጥልቅ መንፈሳዊ ግንዛቤ ሰዎችን ሰላምንና ስርየትን በትጋት እንዲፈልጉ ያደርጋል፤ ያንጊዜም ለነሱ ተስፋ የሚሆን መሠረት ይፈጠራል። እግዚአብሔር በእኛ እንዲደሰትልን፣ የእኛ ትኩረት በክርስቶስ የማስታረቅ ሥራ (የኃጢአት ክፍያ) ተካፋይ መሆን ላይ ሊሆን ይገባል፤ እርሱን የምናስቀይምበት ኃጢአትም እንዲወገድ። ለእግዚአብሔር ፍትሕ የሚያስችለው/የሚያረካው ምንድን ነው? የራሳችን የምንለው የምንከራከርበት ምንም ነገር ስለሌለን በማን ስም ልንመጣ ይገባናል? በምን ጽድቅስ በፊቱ እንቀርባለን? የቀረቡት ሃሳቦች ቅንዓትን ቢያሳዩም እንኳ ድንቁርናን ያሳያሉ። እነርሱ በጣም የበለጸገውንና ውድ የሆነውን ያቀርባሉ። በኃጢአት ሙሉ በሙሉ የጸጸቱና ከእርሱም የሚመጣውን መከራና አደጋ በግልጽ የተገነዘቡ ሰዎች፣ ሰላምንና ስርየትን ለማግኘት ዓለምን ሁሉ (ካላቸው) ይሰጡ ነበር። ሆኖም በትክክል አያቀርቡም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6