የማቴዎስ ወንጌል 26

AMHNIVአማርኛ75 ጥቅሶች11:41 አዳምጥ
አዳምጥ 11:41 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱን፣

2“ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንደሚሆን ታውቃላችሁ፤ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል” አላቸው።

3ከዚህ በኋላ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀያፋ በተባለ ሊቀ ካህን ግቢ ውስጥ ተሰብስበው፤

4በረቀቀ መንገድ ኢየሱስን ለማስያዝና ለማስገደል ተማከሩ።

5ነገር ግን፣ “በሕዝቡ መካከል ረብሻ እንዳይነሣ በበዓል ቀን አይሁን” በማለት ተስማሙ።

6ኢየሱስ በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፣

7አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ አንድ ብልቃጥ የአልባስጥሮስ ሽቶ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች፤ በማእድ ላይ ተቀምጦ ሳለም በራሱ ላይ አፈሰሰችው።

8ደቀ መዛሙርቱ ይህንን በተመለከቱ ጊዜ ተቈጥተው እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሁሉ ብክነት ለምንድ ነው?

9ሽቶው በብዙ ዋጋ ተሽጦ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ሲቻል!”

10ኢየሱስ ይህን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “ይህችን ሴት ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች፤

11ድኾች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔ ግን ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር አልሆንም።

12ሽቶውን በሰውነቴ ላይ በማፍሰሷ፣ እኔን ለቀብር ለማዘጋጀት ነው፤

13እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በዓለም ዙሪያ ሁሉ፣ በየትኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው በመታሰቢያነት ይነገርላታል።”

14ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የነበረውና የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለው ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ፣

15“እርሱን አሳልፌ ብሰጣችሁ እናንተስ ምን ትሰጡኛላችሁ?” አላቸው። እነርሱም ሠላሳ ጥሬ ብር ቈጥረው ሰጡት።

16ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሁዳ፣ ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጥበትን አመቺ ጊዜ ይፈልግ ነበር።

17በቂጣ በዓል የመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “ፋሲካን እንድትበላ የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት።

18እርሱም፣ “ወደ ከተማ ሄዳችሁ እገሌ የተባለውን ሰው፣ ‘መምህር ጊዜዬ ተቃርቦአልና ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን በቤትህ አከብራለሁ ብሏል’ በሉት” አላቸው።

19ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ባዘዛቸው መሠረት የፋሲካን ራት አዘጋጁ።

20በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር በማእድ ተቀመጠ፤

21በመብላት ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው።

22እነርሱም እጅግ አዝነው፣ ተራ በተራ፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ እሆን ይሆን?” አሉት።

23እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሳልፎ የሚሰጠኝ ከእኔ ጋር እጁን ከወጭቱ ውስጥ ያጠለቀው ነው፤

24የሰው ልጅ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ለዚያ ሰው ሳይወለድ ቢቀር ይሻለው ነበር።”

25አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም፣ “መምህር ሆይ፣ እኔ እሆንን?” አለው። እርሱም፣ “አንተ አልህ” አለው።

26እየበሉ ሳሉ፣ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት፣ “እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው።

27ከዚያም ጽዋውን አንሥቶ አመሰገነ፤ ለደቀ መዛሙርቱም በመስጠት እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤

28ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።

29እላችኋለሁ፤ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር በአዲስ መልክ እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ ከእንግዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።”

30መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።

31ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ሁላችሁም በዚህች ሌሊት በእኔ ተሰናክላችሁ ትሄዳላችሁ፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ።’

32ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።”

33ጴጥሮስም መልሶ፣ “ሌሎች በሙሉ ባንተ ምክንያት ቢሰናከሉ እንኳ እኔ በፍጹም አልሰናከልም!” አለው።

34ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ በዛሬዋ ሌሊት ዶሮ ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው።

35ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋር መሞት ቢያስፈልግ እንኳ ከቶ አልክድህም!” አለው። ሌሎቹም ደቀ መዛሙርት በሙሉ እንደዚሁ አሉ።

36ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄደ፤ እነርሱንም፣ “ወደዚያ ሄጄ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው።

37ከእርሱም ጋር ጴጥሮስንና ሁለቱን የዘብዴዎስ ልጆች ይዞ ሄዶ ይተክዝና ይጨነቅ ጀመር፤

38ከዚያም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝናለች፤ ከእኔ ጋር በመትጋት እዚሁ ቈዩ” አላቸው።

39ጥቂት ዕልፍ ብሎ በግንባሩ በመደፋት፣ “አባቴ ሆይ፤ ቢቻል ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ፤ ነገር ግን እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን አንተ እንደምትፈልገው ይሁን” ብሎ ጸለየ።

40ከዚያም ተመልሶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲመጣ፣ ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ፤ ከእኔ ጋር ለአንድ ሰዓት እንኳ መትጋት አቃታችሁን?

41ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው።”

42እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ሄዶ፣ “አባት ሆይ፤ ይህ ሳልጠጣው የማያልፍ ጽዋ ከሆነ፣ ፈቃድህ ይፈጸም” ብሎ ጸለየ።

43እንደ ገናም በመጣ ጊዜ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ስለ ነበር ተኝተው አገኛቸው።

44ትቶአቸውም እንደ ገና በመሄድ ለሦስተኛ ጊዜ ቀደም ብሎ የጸለየውን ጸሎት ደገመ።

45ከዚያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም ዐርፋችሁ ተኝታችኋል? እነሆ፣ ሰዓቱ ቀርቦአል፤ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤

46ተነሡ እንሂድ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝም እየመጣ ነው።”

47በመናገር ላይ እያለ፣ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ዘንድ የተላኩ ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎችም አብረውት ነበሩ።

48ይሁዳም፣ “እኔ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ስለ ነበር፣

49በቀጥታ ወደ ኢየሱስ ሄዶ፣ “መምህር ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት ሳመው።

50ኢየሱስም፣ “ወዳጄ ሆይ፤ የመጣህበትን ፈጽም” አለው። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ቀርበው ኢየሱስን ያዙት፤ አሰሩትም።

51ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው።

52ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ።

53ካስፈለገ አባቴን ብለምነው ከዐሥራ ሁለት ክፍለ ሰራዊት የሚበልጡ መላእክት የማይሰድልኝ ይመስልሃል?

54ይህ ቢሆን ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍት ይሆናል ያሉት ነገር እንዴት ይፈጸማል?”

55በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “ወንበዴ እንደሚይዝ ሰው ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁ? በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ተቀምጬ ሳስተምር አልያዛችሁኝም ነበር፤

56ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው ነቢያት በቅዱሳት መጻሕፍት የተናገሩት ይፈጸም ዘንድ ነው።” በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ጥለውት ሸሹ።

57በዚህ ጊዜ ኢየሱስን የያዙት ሰዎች፣ የኦሪት የሕግ መምህራንና የሕዝብ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደነበሩበት፣ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት።

58ነገር ግን ጴጥሮስ ከርቀት ሆኖ እስከ ሊቀ ካህናቱ ቅጥር ግቢ ይከተለው ነበር፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የሁኔታውን መጨረሻ ለማየት ከጠባቂዎች ጋር ተቀመጠ።

59በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ በሙሉ ኢየሱስን ለማስገደል የሐሰት ማስረጃ ይፈልጉ ነበር፤

60ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢቀርቡም በቂ ማስረጃ አላገኙም፤ በኋላ ግን ሁለት ሰዎች ቀርበው፣

61“ይህ ሰው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፣ በሦስት ቀን ውስጥ መልሼ ልሠራው እችላለሁ’ ብሎአል” በማለት ተናገሩ።

62በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ተነሥቶ በመቆም፣ “እነዚህ ሰዎች ለሚመሰክሩብህ ሁሉ ምንም መልስ አትሰጥምን?” አለው።

63ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም፣ “በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ ንገረን” አለው።

64ኢየሱስም፣ “አንተው ራስህ ብለኸዋል፤ ነገር ግን ለሁላችሁም ልንገራችሁ፤ ወደ ፊት የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው።

65በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ፣ “በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሮአል፤ ከዚህ ሌላ ምን ምስክርነት ያስፈልገናል? በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል መናገሩን እናንተው ራሳችሁ ሰምታችኋአል፤

66ምን ይመስላችኋል?” አላቸው። እነርሱም፣ “ሞት ይገባዋል!” ብለው መለሱ።

67በዚህ ጊዜ ፊቱ ላይ እየተፉ በጡጫ መቱት፤ ሌሎቹም በጥፊ እየመቱት፣

68“ክርስቶስ ሆይ፤ ማነው የመታህ? እስቲ ትንቢት ንገረን!” አሉት።

69ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ ተቀምጦ ሳለ አንዲት የቤት ሠራተኛ ወደ እርሱ ቀርባ፣ “አንተም ከገሊላው ኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው።

70እርሱ ግን፣ “ምን እንደምትናገሪ አላውቅም” በማለት በሁላቸውም ፊት ካደ።

71ከግቢው መውጫ ወደ ሆነው በር ሲያመራ ሌላዋ ሠራተኛ ተመልክታው፣ በዚያ ለነበሩት ሰዎች፣ “ይህ ሰው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበር” አለች።

72እርሱም በመሐላ ቃል፣ “ሰውየውን አላውቀውም!” ሲል ዳግመኛ ካደ።

73ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በዚያ ቆመው የነበሩት ሰዎች ቀርበው ጴጥሮስን፣ “አነጋገርህ ስለሚያጋልጥህ፣ በርግጥ አንተም ከእነርሱ አንዱ ነህ!” አሉት።

74እርሱም እየማለና እየተገዘተ፣ “እኔ ሰውየውን አላውቀውም!” አላቸው። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።

75በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ፣ “ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለው፤ ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።

ማብራሪያ

26:1-5 ጌታችን ስለ መከራው ብዙ ጊዜ ገና ሩቅ እንደሆነ ሲናገር ነበር፤ አሁን ግን ቅርብ እንደሆነ ይናገራል። በዚያው ጊዜም የአይሁድ ሸንጎ በስውር እንዴት ሊገድሉት እንደሚችሉ ተመካከረ። ነገር ግን እግዚአብሔር ሐሳባቸውን ማፍረስ ወደደ። ኢየሱስ፣ እውነተኛው የፋሲካ በግ፣ በዚያው በትክክለኛው ጊዜ ስለ እኛ ሊሰዋ ነበር፤ ሞቱና ትንሣኤውም በይፋ እንዲታወቅ ተደረገ።

፳፮፥፮-፲፫ በክርስቶስ ራስ ላይ የተቀባው ሽቱ የታላቅ ክብርና አክብሮት ምልክት ነበር። በልብ ውስጥ ለእየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ፍቅር ሲኖር፣ ለእርሱ ለመስጠት በጣም ውድ ነው የሚባል ነገር የለም። የክርስቶስ አገልጋዮችና አገልግሎታቸው በበዙ ቁጥር ሲነቀፉ፣ እርሱ ደግሞ ይበልጥ መቀበሉን ያሳያል። ይህ የእምነትና የፍቅር ተግባር እጅግ አስደናቂ ስለነበር፣ የማርያም እምነትና ፍቅር መታሰቢያ ሆኖ፣ ለሁሉም ለሚመጡት ትውልዶችና ወንጌል በሚሰበክበት ስፍራ ሁሉ እንደሚነገርለት ተነግሯል። ይህ ትንቢትም ተፈጽሟል።

26:14-16 ሐዋርያት ተብለው የተጠሩት አስራ ሁለት ብቻ ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ እንደ ሰይጣን ነበረ፤ በእርግጥም ከሰማይ ወዲህ ያለ ማኅበረሰብ ፍጹም ንጹሕ ይሆናል ብለን ልንጠብቅ አይገባም። ሰዎች ሃይማኖተኛነታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ በገለጹ ቁጥር፣ ልባቸው ከእግዚአብሔር ጋር ቅን ካልሆነ፣ ጉዳት የማድረስ ታላቅ ዕድል ይኖራቸዋል። አስተውሉ፤ የክርስቶስ የገዛ ደቀ መዝሙር፣ ትምህርቱንና የአኗኗሩን መንገድ እጅግ በሚገባ ያውቅ የነበረውና ለእርሱ የከዳው ይሁዳ፣ ክህደቱን ለማጽደቅ ይጠቅመው የነበረ ቢሆንም እንኳ፣ በምንም ዓይነት ወንጀል ሊከስሰው አልቻለም። ይሁዳ ምን ፈልጎ ነበር? ጌታው ባለበት ሁሉ ተቀባይነት አልነበረውምን? ኑሮው እንደ ክርስቶስ አልነበረምን? የክፉ ሁሉ ሥር የሆነው የገንዘብ እጦት ሳይሆን የገንዘብ ፍቅር ነው። ያን ክፉ ድርድር ከፈጸመ በኋላ፣ ይሁዳ ንስሐ ለመግባትና ለመሰረዝ ጊዜ ነበረው፤ ነገር ግን ትናንሽ ሐቀኝነት የጎደላቸው ተግባራት ሕሊናን ባደነደኑት ጊዜ፣ ሰዎች ያለምንም ማመንታት ይበልጥ የሚያሳፍርን ነገር ያደርጋሉ።

26:17-25

ልብ በሉ፤ ፋሲካውን የሚበሉበት ስፍራ በክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ተጠቁሞ ነበር። እርሱ ለዓላማው የሚቆሙትን የተደበቁትን ያውቃል፤ እርሱን ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑትን ሁሉ በጸጋ ይጎበኛል። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ። በወንጌል ፋሲካ የክርስቶስ መገኘት እንዲኖራቸው የሚሻ ሁሉ እርሱ የሚለውን ማድረግ አለበት። ለክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በተለይም በፈተና ወቅት ሁልጊዜ ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባቸዋል። ምን ያህል በብርቱ እንደምንፈተን፣ እግዚአብሔርም ምን ያህል ለራሳችን እንደሚተወን አናውቅም፤ ስለዚህ ትዕቢተኞች ከመሆን ይልቅ መፍራት አለብን። የልብ ምርመራና ትጉህ ጸሎት በተለይም ከጌታ እራት በፊት ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ፋሲካችን ሆኖ አሁን ስለ እኛ እንደ ታረደ፣ ንስሐችንንና በደሙ ያለንን እምነት በማደስ፣ እንዲሁም ራሳችንን ለአገልግሎቱ በማስረከብ ይህን በዓል እንድናከብር።

26:26-30 ይህ የጌታ እራት ሥርዓት ለእኛ የፋሲካ እራት ነው፤ በእርሱም እስራኤል ከግብፅ ከወጣችበት መዳን ይልቅ እጅግ ታላቅ የሆነ መዳንን እናስታውሳለን። ውሰዱ፤ ብሉ፤ ክርስቶስ እንደተሰጣችሁ ተቀበሉት፤ የማስተስረያውን ክፍያ ተቀበሉ፣ አጽድቁት፣ ለጸጋውና ለመንግሥቱ ተገዙ። የታየ ምግብ፣ ወይም ሳህኑ የቱንም ያህል ቢያጌጥ፣ አይመግብም፤ መበላት አለበት፤ የክርስቶስ ትምህርትም እንዲሁ ነው። "ይህ ሥጋዬ ነው"፤ ይህም ማለት፣ መንፈሳዊ በሆነ መንገድ፣ ሥጋውን ያመለክታል እንዲሁም ይወክላል። ፀሐይን የምንካፈለው ፀሐይ በእጃችን በመግባቷ ሳይሆን፣ የፀሐይ ጨረሮች በእኛ ላይ በመውረዳቸው ነው፤ እንደዚሁም ክርስቶስን የምንካፈለው ጸጋውን እና ሥጋው በመሰበሩ የተገኙትን የተባረኩ ፍሬዎች በመካፈል ነው። የክርስቶቶስ ደም በወይን ያመለክታል እንዲሁም ይወከላል። ምስጋና አቀረበ፣ ይህም በሥርዓቱ በእያንዳንዱ ክፍል ወደ እግዚአብሔር እንድንመለከት ለማስተማር ነው። ይህን ጽዋም ለደቀ መዛሙርቱ ትእዛዝ በመስጠት ሰጣቸው፡- "ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ።" የኃጢአት ስርየት፣ በጌታ እራት ውስጥ፣ ለሁሉም እውነተኛ አማኞች የሚሰጥ ታላቅ በረከት ነው፤ እርሱም የሌሎች በረከቶች ሁሉ መሠረት ነው። ከእንዲህ ዓይነቱ ኅብረት ይሰናበታል፤ በመጨረሻም ደስ የሚያሰኝ ስብሰባ እንደሚጠብቃቸው ያረጋግጥላቸዋል። "እኔ ከእናንተ ጋር በአዲስነት እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ" የሚለው ቃል፣ ቅዱሳን ከጌታ ኢየሱስ ጋር የሚካፈሏቸውን የወደፊቱ ሁኔታ ደስታዎችና ክብሮች ያመለክታል። ይህ የአባቱ መንግሥት ይሆናል፤ የመጽናናት ወይንም እዚያ ሁልጊዜ አዲስ ይሆናል። ለኃጢአታችን ስርየት የተሰበረውን የክርስቶስን ሥጋና የፈሰሰውን ደሙን ውጫዊ ምልክቶች ስንመለከት፣ ይህ በዓል ሥጋውን እንድንበላ ደሙንም እንድንጠጣ ቃል በቃል እንደሰጠን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለው እናስታውስ።

26:31-35 እንደ ጴጥሮስ እንደነበረው ተገቢ ያልሆነ ራስን መተማመን የመውደቅ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6