የሉቃስ ወንጌል 20

AMHNIVአማርኛ47 ጥቅሶች6:41 አዳምጥ
አዳምጥ 6:41 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1አንድ ቀን ኢየሱስ ሕዝቡን በቤተ መቅደስ ሲያስተምርና ወንጌልን ሲሰብክ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ እርሱ መጡ፤

2እነርሱም፣ “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን እንደሆነ ንገረን፤ ሥልጣንስ የሰጠህ ለመሆኑ እርሱ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት።

3እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ እስቲ መልሱልኝ፤

4የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበር ወይስ ከሰው?”

5እነርሱም እንዲህ ብለው እርስ በርስ ተመካከሩ፤ “ ‘ከሰማይ’ ብንል፣ ‘ታዲያ፣ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤

6‘ከሰው’ ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ ነቢይ መሆኑን ስለ ሚያምኑ በድንጋይ ይወግሩናል።”

7ስለዚህ፣ “ከየት እንደሆነ አናውቅም” ብለው መለሱለት።

8ኢየሱስም፣ “እንግዲያውስ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።

9ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ለሕዝቡ ይነግራቸው ጀመር፤ “አንድ ሰው የወይን ተክል ተከለ፤ ለገበሬዎችም አከራየና ወደ ሌላ አገር ሄዶ ብዙ ጊዜ ቈየ።

10በመከርም ወራት፣ ከወይኑ ፍሬ እንዲልኩለት አገልጋዩን ወደ እነዚህ ገበሬዎች ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን አገልጋዩን ደብድበው ባዶ እጁን ሰደዱት።

11ቀጥሎም ሌላ አገልጋዩን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ ደበደቡት፤ አዋርደውም ባዶ እጁን ሰደዱት።

12አሁንም ቀጥሎ ሦስተኛ አገልጋዩን ላከ፤ ገበሬዎቹም እርሱንም ደግሞ አቊስለው ወደ ውጭ ጣሉት።

13“የወይኑ ተክል ባለቤትም፣ ‘እንግዲህ ምን ላድርግ? እስቲ ደግሞ የምወደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን ያከብሩት ይሆናል’ አለ።

14“ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ይህ እኮ ወራሹ ነው፣ ‘ኑና እንግደለው፤ በዚህም ርስቱ የእኛ ይሆናል’ እየተባባሉ ተመካከሩ፤

15ከወይኑም ተክል ቦታ ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። “እንግዲህ የወይኑ ተክል ባለቤት ምን ያደርጋቸዋል?

16መጥቶ እነዚያን ገበሬዎች ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም ተክል ቦታ ለሌሎች ይሰጣል።” ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ፣ “እንዲህ ያለውንስ አያምጣው” አሉ።

17ኢየሱስም ወደ እነርሱ ተመልክቶ እንዲህ አላቸው፤ “ ‘ታዲያ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ’ ተብሎ የተጻፈው ትርጒሙ ምንድን ነው?

18በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩም በላዩ የሚወድቅበት ሁሉ ይደቃል።”

19ጸሐፍትና የካህናት አለቆችም ይህንን ምሳሌ የተናገረው በእነርሱ ላይ መሆኑን ስላወቁ፣ በዚያኑ ሰዓት ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ።

20ኢየሱስን አሳልፈው ለገዥው ኀይልና ሥልጣን ለመስጠት፣ ከአፉ በሚወጣ ቃል ለማጥመድ ይከታተሉት ነበር፤ ስለዚህም ጻድቃን መስለው የሚቀርቡ ሰላዮችን ላኩበት።

21ሰላዮቹም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደምታስተምርና ለማንም እንደማታደላ እናውቃለን።

22ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”

23እርሱ ግን ተንኰላቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤

24“እስቲ አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ በላዩ ያለው የማን መልክና ጽሕፈት ነው?”

25እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” ብለው መለሱለት። እርሱም፣ “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው።

26ስለዚህ በተናገረው ቃል በሕዝቡ ፊት ሊያጠምዱት አልቻሉም፤ በመልሱም ተገርመው ዝም አሉ።

27ትንሣኤ ሙታን የለም ከሚሉት ሰዱቃውያን አንዳንዶቹ ወደ ኢየሱስ መጥተው ጥያቄ አቀረቡለት፤

28እንዲህም አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንድ ሰው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ ወንድሙ መበለቲቱን አግብቶ ልጆች በመውለድ ለወንድሙ ዘር እንዲተካ ሙሴ ጽፎልናል።

29ታዲያ፣ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤

30ሁለተኛውም እንደዚሁ፤

31ሦስተኛው ደግሞ አገባት፤ ሰባቱም እንዲሁ እያሉ አግብተዋት ልጆች ሳይወልዱ ሞቱ።

32በመጨረሻም ሴትዮዋ ሞተች።

33እንግዲህ ሰባቱም ስላገቧት፣ በትንሣኤ ጊዜ የማን ሚስት ትሆናለች?”

34ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ፤ ይጋባሉም፤

35የሚመጣውን ዓለምና የሙታንን ትንሣኤ ማግኘት የሚገባቸው ግን አያገቡም፤ አይጋቡም፤

36እንደ መላእክትም ስለሆኑ ከዚያ በኋላ አይሞቱም፤ የትንሣኤ ልጆች ስለ ሆኑም የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።

37ሙሴ ስለ ቊጥቋጦ በተጻፈው ታሪክ ውስጥ ጌታን፣ ‘የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ’ በማለቱ ሙታን እንደሚነሡ ያሳያል፤

38ሁሉም ለእርሱ ሕያዋን ስለሆኑ፣ እርሱ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አይደለም።”

39አንዳንድ ጸሐፍትም፣ “መምህር ሆይ፤ መልካም ተናገርህ” አሉት።

40ከዚህ በኋላ አንድ ሰው እንኳ ሊጠይቀው አልደፈረም።

41ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ሰዎች ክርስቶስን እንዴት የዳዊት ልጅ ነው ይሉታል?

42ምክንያቱም ራሱ ዳዊት በመዝሙራት መጽሐፉ እንዲህ ብሏል፤ “ ‘ጌታ ጌታዬን፣ “በቀኜ ተቀመጥ፤

43እኔ ጠላቶችህን፣ ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ።” ’

44እንግዲህ ዳዊት እርሱን፣ ‘ጌታ’ ብሎ ሲጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል?”

45ሕዝቡ ሁሉ እየሰሙትም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፤

46“ዘርፋፋ ቀሚስ ለብሰው መዞር ከሚወዱ፣ በገበያ ቦታ ሰላምታ ከሚሹና በምኵራብ የከበሬታ መቀመጫ፣ በግብዣ ቦታም የክብር ስፍራ ከሚፈልጉ፣ ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤

47እነርሱም የመበለቶችን ቤት የሚያራቊቱ ናቸው፤ ለታይታ ብለውም ጸሎታቸውን ያስረዝማሉ፤ እነዚህ የከፋ ፍርድ ይጠብቃቸዋል።”

ማብራሪያ

ሉቃስ 20:1-8

ሰዎች ብዙውን ጊዜ የመገለጥን ማስረጃዎችና የወንጌልን እውነት ለመመርመር ያስመስላሉ፤ በእርግጥ ግን ለራሳቸው አለማመንና አለመታዘዝ ሰበብ የሚፈልጉ ብቻ ናቸው። ክርስቶስም እነዚህን ካህናትና ጸሐፍት ስለ ዮሐንስ ጥምቀት በቀላል ጥያቄ መለሰላቸው፤ ይህም ተራው ሕዝብ ሊመልሰው የሚችል ነበር። ሁሉም ከሰማይ እንደሆነ ያውቁ ነበር፤ በውስጡም ምንም ምድራዊ ዝንባሌ አልነበረውም። ያላቸውን እውቀት የሚቀብሩ ሰዎች በትክክል ተጨማሪ እውቀት ይከለከላሉ። ዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ እንደሆነ እያወቁ በእርሱ ያላመኑትንና የሚያውቁትንም እውነት ያልተናዘዙትን ሰዎች ስለ ስልጣኑ መልስ ለመስጠት ክርስቶስ እምቢ ማለቱ ፍትሐዊ ነበር።

20:9-19 ክርስቶስ ይህን ምሳሌ የተናገረው ስልጣኑን ላለመቀበል በቆረጡ ሰዎች ላይ ነበር፤ ማስረጃው እጅግ ብዙ ቢሆንም እንኳ። በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው ጥላቻ፣ አገልግሎቱንም በመጥላት፣ ያለ ምንም ገደብ እንደ ምኞታቸው ለመኖር በመሻት፣ ነቢያትን የገደሉትንና ክርስቶስን የሰቀሉትን አይሁድን የሚመስሉ ስንትና ስንት ሰዎች አሉ! የእግዚአብሔር ቃል የተቸራቸው ሁሉ፣ የተሰጣቸውን ጥቅም በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ይጠንቀቁ። ወልድን ለሚጥሉ (ለሚከዱትም)፣ እርሱን እንደሚያከብሩ እየተናገሩ (እየመሰሉ) ፍሬን በወቅቱ ለማይሰጡትም ሁሉ፣ የመጨረሻው ፍርድ እጅግ አስከፊ ይሆናል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6

AMHEVG አንድ ቀንም ሕዝቡን በመቅደስ ሲያስተምር ወንጌልንም ሲሰብክላቸው፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ከሽማግሌዎች ጋር ወደ እርሱ ቀረቡና፦ አማርኛ ENGNIV One day as he was teaching the people in the temple courts and preaching the gospel, the chief priests and the teachers… English BCV ሓደ መዓልቲ ኢየሱስ፥ ኣብ ቤተ መቕደስ ንህዝቢ ኽምህርን፥ ወንጌል ክሰብኽን እንተሎ፥ ሊቃነ ካህናትን መምህራን ሕግን፥ ምስ ዓበይቲ ህዝቢ ኾይኖም ናብኡ መፂኦም፥ ትግርኛ GAZBIB Gaaf tokko Yesus mana qulqullummaa keessatti namoota barsiisaa, wangeelas lallabaa utuu jiruu, luboonni warri angafoonn… Afaan Oromoo BCV GIZ ወእምዝ አሐተ ዕለተ እንዘ ይሜህሮሙ ለሕዝብ በምኵራብ ወይነግሮሙ ቆሙ ላዕሌሁ ሊቃነ ካህናት ወጸሐፍት ወረበናት። giz GAZGAZ Gaaf tokko Yesus mana qulqullummaa keessatti namoota barsiisaa, wangeelas lallabaa utuu jiruu, luboonni warri angafoonn… Afaan Oromoo BCV aksum ሓደ መዓልቲ ኢየሱስ፥ ኣብ ቤተ መቕደስ ንህዝቢ ኽምህርን፥ ወንጌል ክሰብኽን እንተሎ፥ ሊቃነ ካህናትን መምህራን ሕግን፥ ምስ ዓበይቲ ህዝቢ ኾይኖም ናብኡ መፂኦም፥ ትግርኛ SWAHSUV Ikawa siku moja, alipokuwa akiwafundisha watu hekaluni, na kuihubiri habari njema, wakuu wa makuhani na waandishi pamoj… Kiswahili