የሉቃስ ወንጌል 1

AMHNIVአማርኛ80 ጥቅሶች10:28 አዳምጥ
አዳምጥ 10:28 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በእኛ መካከል ስለ ተፈጸሙት ነገሮች ብዙዎች ታሪኩን የተቻላቸውን ያህል ጽፈውት ይገኛል፤

2ይህም ታሪክ ከመጀመሪያው አንሥቶ የዐይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የነበሩት ያስተላለፉልን ነው።

3ክቡር ቴዎፍሎስ ሆይ፤ እኔም በበኩሌ ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ከመረመርሁ በኋላ፣ ታሪኩን ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ፤

4ይህንንም የማደርገው የተማርኸው ነገር እውነተኛ መሆኑን እንድታውቅ ነው።

5በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን፣ ከአብያ የክህነት ምድብ የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱ ኤልሳቤጥም ከአሮን ነገድ ነበረች።

6ሁለቱም የጌታን ትእዛዝና ሥርዐት ሁሉ ጠብቀው ያለ ነቀፋ የሚኖሩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤

7ይሁን እንጂ ኤልሳቤጥ መካን በመሆኗ ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜ የገፉ ነበሩ።

8አንድ ቀን ዘካርያስ በምድቡ ተራ፣ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት በሚያገለግልበት ጊዜ፣

9በሥርዐተ ክህነቱ መሠረት፣ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን በዕጣ ተመረጠ።

10ዕጣን በሚታጠንበትም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ሆኖ ይጸልይ ነበር።

11የጌታም መልአክ ከዕጣን መሠዊያው በስተቀኝ ቆሞ ታየው።

12ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሀትም ተዋጠ።

13መልአኩ ግን እንዲህ አለው፤ “ዘካርያስ ሆይ፤ አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቶአል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ።

14በእርሱ ተድላና ደስታ ታገኛለህ፤ ብዙዎችም እርሱ በመወለዱ ደስ ይላቸዋል፤

15በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና። የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ በእናቱም ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል።

16ከእስራኤልም ሰዎች ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤

17የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፣ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ፣ ለጌታ የተገባ ሕዝብ ለማዘጋጀት በኤልያስ መንፈስና ኀይል በጌታ ፊት ይሄዳል።”

18ዘካርያስም መልአኩን፣ “ይህን በምን አውቃለሁ? እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜ ገፍታለች” አለው።

19መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህን እነግርህና ይህን የምሥራች አመጣልህ ዘንድ ተልኬአለሁ፤

20እነሆ፤ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፣ ይህም እስከሚፈጸምበት ቀን ድረስ ድዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።”

21በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ዘካርያስ ከቤተ መቅደሱ ሳይወጣ ለምን እንደ ዘገየ በመገረም ይጠባበቅ ነበር።

22ከወጣ በኋላም ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በምልክት ከመጥቀስ በስተቀር መናገር ባለመቻሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ።

23ዘካርያስም የአገልግሎቱ ወቅት በተፈጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

24ከዚህ በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ አምስት ወራትም ራሷን ሰወረች፤

25እርሷም፣ “ጌታ በምሕረቱ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ሊያስወግድልኝ ተመልክቶ በዚህ ጊዜ ይህን አድርጎልኛል” አለች።

26በስድስተኛው ወር፣ እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ናዝሬት ከተማ ላከው፤

27የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።

28መልአኩም እርሷ ወዳለችበት ገብቶ፣ “እጅግ የተወደድሽ ሆይ፤ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት።

29ማርያምም በንግግሩ እጅግ በጣም ደን ግጣ፣ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” እያለች ነገሩን ታሰላስል ጀመር፤

30መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ።

31እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ።

32እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤

33በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።”

34ማርያምም መልአኩን፣ “እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው።

35መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፤ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።

36እነሆ፤ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም በስተ እርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን የተባለችውም ስድስተኛ ወሯን ይዛለች፤

37ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።”

38ማርያምም፣ “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። ከዚያም መልአኩ ተለይቶአት ሄደ።

39ማርያምም በዚያው ሰሞን በፍጥነት ተነሥታ ወደ ደጋው አገር፣ ወደ አንድ የይሁዳ ከተማ ሄደች፤

40ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች።

41ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤

42ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው።

43ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ?

44እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሎአልና።

45ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ የተባረከች ናት!”

46ማርያምም እንዲህ አለች፤ “ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤

47መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች፤

48እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቶአልና። ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤

49ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅ ነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤

50ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።

51በክንዱ ብርቱ ሥራ ሠርቶአል፤ በልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኖአቸዋል፤

52ገዢዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአቸዋል፤ ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጎአቸዋል፤

53የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአቸዋል፤ ሀብታሞችን ግን ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል፤

54ምሕረቱን በማስታወስ፣ ባሪያውን እስራኤልን ረድቶአል፤

55ይህም ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣ ለአብርሃምና ለዘሩ ያለውን ለዘላለም ለመጠበቅ ነው።”

56ማርያምም ሦስት ወር ያህል ኤልሳቤጥ ዘንድ ከቈየች በኋላ ወደ ቤቷ ተመለሰች።

57የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ቀን ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች።

58ጎረቤቶቿና ዘመዶቿም ጌታ ታላቅ ምሕረት እንዳደረገላት ሰሙ፤ የደስታዋም ተካፋዮች ሆኑ።

59በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ፈለጉ፤

60እናቱ ግን፣ “አይሆንም፤ ዮሐንስ መባል አለበት” አለች።

61እነርሱም፣ “ከዘመዶችሽ በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም” አሏት።

62አባቱንም ምን ስም ሊያወጣለት እንደሚፈልግ በምልክት ጠየቁት።

63እርሱም መጻፊያ ሰሌዳ እንዲሰጡት ለምኖ፣ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም በነገሩ ተደነቁ።

64ወዲያውም አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱ ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ መናገር ጀመረ።

65ጎረቤቶቹም ሁሉ በፍርሀት ተሞሉ፤ ይህም ሁሉ ነገር በደጋማው የይሁዳ ምድር ሁሉ ተወራ።

66ይህንም የሰሙ ሁሉ፣ “ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ነገሩን በልባቸው ያዙ፤ የጌታ እጅ በርግጥ ከእርሱ ጋር ነበርና።

67የሕፃኑም አባት ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፤

68“የእስራኤል አምላክ፣ ጌታ ይመስገን፤ መጥቶ ሕዝቡን ተቤዥቶአልና።

69በባሪያው በዳዊት ቤት፣ የድነት ቀንድ አስነሥቶልናል፤

70ይህም ጥንት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረው፣

71ማዳኑም ከጠላቶቻችንና፣ ከተፃራሪዎቻችን ሁሉ እጅ ነው፤

72ይህንም ያደረገው ለአባቶቻችን ምሕረቱን ለማሳየት፣ ቅዱስ ኪዳኑን ለማስታወስ፣

73ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ለማሰብ፣

74ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶ፣ ያለ ፍርሀት እንድናገለግለው፣

75በዘመናችንም ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ ሊያቆመን ነው።

76ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፤ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ የጌታን መንገድ ለማዘጋጀት በፊቱ ትሄዳለህና፤

77የኀጢአታቸውን ስርየት ከማግኘታቸው የተነሣ፤ ለሕዝቡ የመዳንን ዕውቀት ትሰጥ ዘንድ፣

78ከአምላካችንም በጎ ምሕረት የተነሣ፣ የንጋት ፀሓይ ከሰማይ ወጣችልን፤

79ይኸውም በጨለማ ለሚኖሩት፣ በሞት ጥላ ውስጥም ላሉት እንዲያበራና፣ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ እንዲመራ ነው።”

80ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤልም ሕዝብ በይፋ እስከታየበት ቀን ድረስ በበረሓ ኖረ።

ማብራሪያ

1:1-4. ሉቃስ ክርስቲያኖች እርስ በእርሳቸው በሰላም ሊለያዩባቸው የሚችሉትንና በራሳቸውም ሊጠራጠሩባቸው የሚችሉትን ነገሮች አይጽፍም፤ ነገር ግን በእርግጠኝነት መታመን ያለባቸውንና ያሉትን እውነታዎች ይጽፋል። የክርስቶስ ትምህርት፣ ጥበበኞችና ከሰዎች ሁሉ የላቁት ነፍሳቸውን በሙሉ እምነትና በእርካታ የጣሉበት ነው። ተስፋዎቻችን የተመኩባቸው ታላላቆቹ ክስተቶችም ከመጀመሪያው የዓይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት፣ ግንዛቤያቸውም በመለኮታዊ ተመስጦ ፍጹም የሆነላቸው ሰዎች ዘንድ ተመዝግበዋል።

1:5-25 የዮሐንስ መጥምቅ አባትና እናት እንደ ሁሉም ሰዎች ኃጢአተኞች ነበሩና ልክ እንደ ሌሎች ሰዎች በዚያው መንገድ ጸድቀዋል እንዲሁም ድነዋል፤ ነገር ግን በቅድስናቸውና በታማኝነታቸው እጅግ የላቁ ነበሩ። ልጅ አልነበራቸውም ነበር፤ ኤልሳቤጥም በእርጅናዋ ልጅ እንደምትወልድ ሊጠበቅ አልቻለም ነበር። ዘካርያስ በመቅደሱ ዕጣን በሚያጥንበት ጊዜ መላው ሕዝብ ከውጭ ሆነው ይጸልዩ ነበር። ወደ እግዚአብሔር የምናቀርባቸው ጸሎቶች ሁሉ ተቀባይነት ያላቸውና ምላሽ የሚያገኙት በላይ ባለው በእግዚአብሔር መቅደስ በክርስቶስ ምልጃ ብቻ ነው። ካልጸለይን፣ በመንፈሳችን ካልጸለይን እንዲሁም በጸሎት ጽኑዕ ካልሆንን በዚህ ውስጥ ድርሻ ልንጠብቅ አንችልም። ምርጥ ጸሎቶቻችንም ቢሆኑ ተቀባይነትን እንደሚያገኙና የሰላም ምላሽን እንደሚያመጡ ልንጠብቅ አንችልም፤ ነገር ግን በዘላለም ሕያው በሆነውና ዘወትር በሚማልደው በክርስቶስ አማካኝነት ብቻ ነው። ዘካርያስ ብዙ ጊዜ ያቀረባቸው ጸሎቶች የሰላም ምላሽ አግኝተዋል። የእምነት ጸሎቶች በሰማይ ተመዝግበዋል፤ አይረሱም። ወጣት ሳለን ዓለምን ስንገባ ያቀረብናቸው ጸሎቶች አርጅተን ዓለምን ስንለቅ ምላሽ ሊያገኙ ይችላሉ። ለጸሎት ምላሽ የሚሰጡ ምህረቶች በእጥፍ ጣፋጭ ናቸው። ዘካርያስ በእርጅናው ወንድ ልጅ ያገኛል፤ እርሱም ብዙ ነፍሳትን ወደ እግዚአብሔር በመመለስ ረገድ ወሳኝ ይሆናል እንዲሁም የክርስቶስን ወንጌል ለመቀበል ያዘጋጃቸዋል። በድፍረት፣ በቅንዓት፣ በቅድስና እንዲሁም ለምድራዊ ፍላጎቶችና ደስታዎች የሞተ ልቦና ይዞ ከእርሱ በፊት ይሄዳል። የማይታዘዙትና ዓመፀኞቹ የጻድቅ አባቶቻቸውን ጥበብ እንዲመለሱ ይደረጋሉ፤ ይልቁንም፣ በመካከላቸው ወደሚመጣው ወደዚያ ጻድቅ የሆነው አካል ጥበብ ትኩረት እንዲሰጡ ይደረጋሉ። ዘካርያስ መልአኩ የተናገረውን ሁሉ ሰማ፤ ነገር ግን አለማመኑ ተናገረ። ዲዳ በማድረግ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ በጽድቅ አደረገበት፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቃል ተቃውሞ ነበርና። በእኛ ላይ የእግዚአብሔርን ትዕግስት ልናደንቅ እንችላለን። እግዚአብሔር በእርሱ ላይ በደግነት ፈጸመበት፤ ምክንያቱም በዚህ መንገድ ከእንግዲህ የማያምኑ፣ የሚጠራጠሩ ቃላትን ከመናገር አግዶታል። በዚህም እግዚአብሔር እምነቱን አጸናለት። ለኃጢአታችን የምንቀበላቸው ተግሳጾች የእግዚአብሔርን ቃል ይበልጥ እንድናምን ካደረጉን የምናማርርበት ምንም ምክንያት የለንም። እውነተኛ አማኞችም እንኳ ባለማመን እግዚአብሔርን ክብሩን ለመቀነስ ይዳርጋሉ፤ አለዚያ ግን በደስታና በአመስጋኝነት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ በነበረበት ጊዜ አፋቸው በዝምታና በድንጋጤ ይዘጋል። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር በሚያደርገው ጸጋ የተሞላ ተግባር በእኛ ላይ ያለውን ጸጋ የተሞላ አሳቡን ልንመለከት ይገባናል። በምሕረትና በሞገስ ተመልክቶናል፤ ስለዚህም እንደዚህ አድርጎብናል።

ሉቃስ 1:26-38

እዚህ ጋር የጌታችንን እናት ታሪክ እናገኛለን፤ ምንም እንኳን ለእርሷ መጸለይ ባይገባንም፣ ለእርሷ ግን እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባናል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6