የሉቃስ ወንጌል 18

AMHEVGአማርኛ43 ጥቅሶች5:09 አዳምጥ
አዳምጥ 5:09 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንዲገባቸው የሚል ምሳሌን ነገራቸው፥

2እንዲህ ሲል፦ “በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበረ።

3በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፥ ወደ እርሱም እየመጣች፦ ‘ከባላጋራዬ ፍረድልኝ፡’ ትለው ነበር።

4አያሌ ቀንም አልወደደም፤ ከዚህ በኋላ ግን በልቡ፦ ‘ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ ሰውንም ባላፍር፥

5ይህች መበለት ስለምታደክመኝ ሁልጊዜም እየመጣች እንዳታውከኝ እፈርድላታለሁ፡’ አለ።”

6ጌታም አለ፦ “ዓመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ።

7እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን?

8እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?”

9ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥ እንዲህ ሲል፦

10“ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ።

11ፈሪሳዊም ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ፦ ‘እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤

12በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ፡’ አለ።

13“ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን፦ ‘አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ፡’ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።

14እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል።”

15እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ደግሞ ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም አይተው ገሠጹአቸው።

16ኢየሱስ ግን ሕፃናትን ወደ እርሱ ጠርቶ፦ “ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው አትከልክሉአቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና።

17እውነት እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም፡” አለ።

18ከአለቆችም አንዱ፦ “ቸር መምህር፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” ብሎ ጠየቀው።

19ኢየሱስም፦ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም።

20ትእዛዛቱን ታውቃለህ፥ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አባትህንና እናትህን አክብር፡” አለው።

21እርሱም፦ “ይህን ሁሉ ከሕፃንናቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፡” አለ።

22ኢየሱስም ይህን ሰምቶ፦ “አንዲት ገና ቀርታሃለች፤ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ፡” አለው።

23እርሱ ግን ይህን ሰምቶ እጅግ ባለ ጠጋ ነበርና ብዙ አዘነ።

24ኢየሱስም ብዙ እንዳዘነ አይቶ እንዲህ አለ፦ “ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል።

25ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ሊገባ ይቀላል።”

26የሰሙትም፦ “እንግዲህ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ።

27እርሱ ግን፦ “በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል” አለ።

28ጴጥሮስም፦ “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፡” አለ።

29እርሱም አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ቤትን ወይም ወላጆችን ወይም ወንድሞችን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን የተወ፥

30በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።”

31አሥራ ሁለቱንም ወደ እርሱ አቅርቦ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተጻፈው ሁሉ ይፈጸማል።

32ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና፥ ይዘብቱበትማል ያንገላቱትማል ይተፉበትማል፤

33ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።”

34እነርሱም ከዚህ ነገር ምንም አላስተዋሉም፥ ይህም ቃል ተሰውሮባቸው ነበር፥ የተናገረውንም አላወቁም።

35ወደ ኢያሪኮም በቀረበ ጊዜ አንድ ዕውር እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ነበር።

36ሕዝብም ሲያልፍ ሰምቶ፦ “ይህ ምንድር ነው?” ብሎ ጠየቀ።

37እነርሱም፦ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ያልፋል፡” ብለው አወሩለት።

38እርሱም፦ “የዳዊት ልጅ፥ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ፡” እያለ ጮኸ።

39በስተ ፊት ይሄዱ የነበሩትም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፦ “የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ፡” እያለ አብዝቶ ጮኸ።

40ኢየሱስም ቆሞ ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ። በቀረበም ጊዜ፦

41“ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ አይ ዘንድ ነው፡” አለው።

42ኢየሱስም፦ “እይ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።

43በዚያን ጊዜም አየ፥ እግዚአብሔርንም እያከበረ ተከተለው። ሕዝቡም ሁሉ አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

ማብራሪያ

፲፰፥፩-፰ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ጸሎተኞች ናቸው። በዚህ ክፍል ለመንፈሳዊ በረከቶች በትጋትና በጽናት መጸለይ ትምህርት ይሰጣል። የመበለቲቱ ትጋት ከዓመፀኛው ዳኛ ዘንድ እንኳን አሳመነችው፤ ይህ ደግሞ ይበልጥ በእርሷ ላይ እንዳያነሳሳው ብላ ትሰጋ ይሆናል፤ ነገር ግን የእኛ ትጉህ ጸሎት አምላካችንን ደስ ያሰኛል። እስከ መጨረሻውም ድረስ ስለ እምነት ድካም ለሚቀርበው ተመሳሳይ ቅሬታ ምክንያት ይኖራል።

ሉቃስ 18:9-14 ይህ ምሳሌ ራሳቸውን ጻድቃን እንደሆኑ አድርገው በራሳቸው ይመኩ የነበሩትንና ሌሎችንም ይንቁ የነበሩትን ለማሳመን ነበር። እግዚአብሔር በቅዱስ ሥርዓት (በጸሎትም ሆነ በሌላ አምልኮ) ወደ እርሱ ስንቀርብ በምን መንፈስና ዓላማ እንደምንመጣ ያያል። ፈሪሳዊው የተናገረው ነገር በራሱ ጻድቅ እንደሆነ በራሱ ይመካ እንደነበር ያሳያል። ምናልባትም ከከባድና ነውር ከሚያስከትሉ ኃጢአቶች ነፃ እንደነበር ልንገምት እንችላለን። ይህ ሁሉ መልካም እና የሚያስመሰግን ነበር። ከዚህ ፈሪሳዊ ጽድቅ በታች የሆኑ ሰዎች ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ነው፤ ሆኖም ግን እሱ አልተወደደም (አልተቀበለም)፤ ለምንስ አልተቀበለም? ወደ ቤተ መቅደስ የሄደው ለመጸለይ ነበር፤ ነገር ግን በራሱና በራሱ መልካምነት ተሞልቶ ነበር፤ የእግዚአብሔርን ሞገስና ጸጋ መጠየቅ እንደሚያስፈልገው አላሰበም። እንግዲህ ለእግዚአብሔር ኩሩ አምልኮ (ጸሎት) ከማቅረብና ሌሎችንም ከመናቅ እንጠንቀቅ።

የቀረጥ ሰብሳቢው ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎት በትህትና፣ በኃጢአት ንስሐና ወደ እግዚአብሔር ባለው ናፍቆት የተሞላ ነበር። ጸሎቱ አጭር ቢሆንም ዓላማ ያለው ነበር፤ እንዲህም አለ፦ ‘አምላክ ሆይ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ።’ ይህ አጭር ጸሎት እንደተመለሰ ጸሎት ተመዝግቦልን በመገኘቱና፣ የጸለየውም ወደ ቤቱ ጸድቆ እንደሄደ እርግጠኞች በመሆናችን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ እኛም እንደ እርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከጸለይነው እንዲሁ እንጸድቃለንና። እርሱ በተፈጥሮ፣ በተግባርም ኃጢአተኛ መሆኑንና በእግዚአብሔር ፊት ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል። ጥገኝነቱ በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ብቻ ነበር፤ በዚያ ላይ ብቻም ተማምኖ ነበር። የእግዚአብሔር ክብርም ትዕቢተኞችን መቃወም፣ ለትሑታንም ጸጋን መስጠት ነው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6