የሉቃስ ወንጌል 18

AMHNIVአማርኛ43 ጥቅሶች6:34 አዳምጥ
አዳምጥ 6:34 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ደቀ መዛሙርቱ ሳይታክቱ ሁል ጊዜ መጸለይ እንደሚገባቸው ለማሳየት ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤

2እንዲህም አላቸው፤ “በአንዲት ከተማ የሚኖር እግዚአብሔርን የማይፈራና ሰውን የማያከብር አንድ ዳኛ ነበረ።

3በዚያችው ከተማ የምትኖር አንዲት መበለት ነበረች፤ እርሷ፣ ‘ከባላጋራዬ ጋር ስላለብኝ ጒዳይ ፍረድልኝ’ እያለች ወደ እርሱ ትመላለስ ነበር።

4“ዳኛውም ለተወሰነ ጊዜ አልተቀበላትም ነበር፤ በኋላ ግን በልቡ እንዲህ አለ፤ ‘ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ፣ ሰውንም ባላከብር፣

5ይህች መበለት ስለ ምትጨቀጭቀኝ እፈርድላታለሁ፤ አለበለዚያ ዘወትር እየተመላለሰች ታሰለቸኛለች።”

6ጌታም እንዲህ አለ፤ “ዐመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ።

7እግዚአብሔርስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? ከመጠን በላይስ ችላ ይላቸዋልን?

8እላችኋለሁ፤ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ እምነትን ያገኝ ይሆንን?”

9ራሳቸውን እንደ ጻድቃን በመቊጠር ለሚመኩና ሌሎቹን በንቀት ዐይን ለሚመለከቱ ሰዎች እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤

10“ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፣ አንዱ ፈሪሳዊ፣ ሌላው ቀረጥ ሰብሳቢ ነበሩ።

11ፈሪሳዊውም ቆሞ ስለ ራሱ እንዲህ ይጸልይ ነበር፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ እንደ ሌላው ሰው ሁሉ ቀማኛ፣ ዐመፀኛ፣ አመንዝራ፣ ይልቁንም እንደዚህ ቀረጥ ሰብሳቢ ባለመሆኔ አመሰግንሃለሁ፤

12በሳምንት ሁለት ጊዜ እጾማለሁ፤ ከማገኘውም ሁሉ ዐሥራት አወጣለሁ።”

13“ቀረጥ ሰብሳቢው ግን በርቀት ቆሞ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ማየት እንኳ አልፈለገም፤ ነገር ግን ደረቱን እየደቃ፣ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ኀጢአተኛውን ማረኝ’ ይል ነበር።

14“እላችኋለሁ፤ ከፈሪሳዊው ይልቅ ይኸኛው በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ጻድቅ ተቈጥሮ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላልና፤ ራሱን ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ግን ከፍ ይላል።”

15ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ ያመጡ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ባዩ ጊዜ ገሠጿቸው።

16ኢየሱስ ግን ሕፃናቱን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አለ፤ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ፍቀዱላቸው፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና።

17እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።”

18ከአይሁድ አለቆች አንዱ፣ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” ሲል ጠየቀው።

19ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም፤

20‘አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለውን ትእዛዝ ታውቃለህ።”

21ሰውየውም፣ “እነዚህንማ ከልጅነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ” አለው።

22ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ፣ “እንግዲያውስ አንድ ነገር ይቀርሃል፤ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ መዝገብ ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው።

23ሰውየው ግን ይህን ሲሰማ፣ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው በጣም ዐዘነ።

24ኢየሱስም ሰውየውን ተመልክቶ እንዲህ አለ፤ “ብዙ ሀብት ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው?

25ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል።”

26ይህን የሰሙ ሰዎችም፣ “ታዲያ፣ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ።

27ኢየሱስም፣ “በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል” አለ።

28ጴጥሮስም፣ “እነሆ፤ እኛ ያለንን ሁሉ ትተን ተከትለንሃል” አለው።

29ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ለእግዚአብሔር መንግሥት ብሎ ቤቱን ወይም ሚስቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም ወላጆቹን ወይም ልጆቹን የተወ፣

30በዚህ ዘመን ብዙ ዕጥፍ፣ በሚመጣውም ዘመን የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።”

31ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻ ወስዶ እንዲህ አላቸው፤ “እንግዲህ ወደ ኢየሩሳሌም ልንወጣ ነው፤ ነቢያት ስለ ሰው ልጅ የጻፉትም ሁሉ ይፈጸማል።

32ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ እነርሱም ያፌዙበታል፤ ያንገላቱታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል።

33እርሱም በሦስተኛው ቀን ከሙታን ይነሣል።”

34ደቀ መዛሙርቱ ግን ከዚህ ሁሉ የተረዱት አንድም ነገር አልነበረም፤ አባባሉም ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለ ምን እንደ ተናገረም አላወቁም።

35ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ በቀረበ ጊዜ፣ አንድ ዐይነ ስውር መንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር።

36ዐይነ ስውሩም ሕዝቡ በዚያ ሲያልፍ ሰምቶ ስለ ሁኔታው ጠየቃቸው።

37እነርሱም፣ “የናዝሬቱ ኢየሱስ በዚህ እያለፈ ነው” ብለው ነገሩት።

38እርሱም፣ “የዳዊት ልጅ፣ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ ጮኸ።

39ከፊት የሚሄዱ ሰዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ አብዝቶ ጮኸ።

40ኢየሱስም ቆም ብሎ ሰውየውን ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ፤ ወደ እርሱም በቀረበ ጊዜ፣

41“ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው። ዐይነ ስውሩም፣ “ጌታ ሆይ፤ ማየት እፈልጋለሁ” አለው።

42ኢየሱስም፣ “እይ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።

43ሰውየውም ወዲያውኑ ማየት ቻለ፤ እግዚአብሔርንም እያከበረ ኢየሱስን ተከተለው። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

ማብራሪያ

፲፰፥፩-፰ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ጸሎተኞች ናቸው። በዚህ ክፍል ለመንፈሳዊ በረከቶች በትጋትና በጽናት መጸለይ ትምህርት ይሰጣል። የመበለቲቱ ትጋት ከዓመፀኛው ዳኛ ዘንድ እንኳን አሳመነችው፤ ይህ ደግሞ ይበልጥ በእርሷ ላይ እንዳያነሳሳው ብላ ትሰጋ ይሆናል፤ ነገር ግን የእኛ ትጉህ ጸሎት አምላካችንን ደስ ያሰኛል። እስከ መጨረሻውም ድረስ ስለ እምነት ድካም ለሚቀርበው ተመሳሳይ ቅሬታ ምክንያት ይኖራል።

ሉቃስ 18:9-14 ይህ ምሳሌ ራሳቸውን ጻድቃን እንደሆኑ አድርገው በራሳቸው ይመኩ የነበሩትንና ሌሎችንም ይንቁ የነበሩትን ለማሳመን ነበር። እግዚአብሔር በቅዱስ ሥርዓት (በጸሎትም ሆነ በሌላ አምልኮ) ወደ እርሱ ስንቀርብ በምን መንፈስና ዓላማ እንደምንመጣ ያያል። ፈሪሳዊው የተናገረው ነገር በራሱ ጻድቅ እንደሆነ በራሱ ይመካ እንደነበር ያሳያል። ምናልባትም ከከባድና ነውር ከሚያስከትሉ ኃጢአቶች ነፃ እንደነበር ልንገምት እንችላለን። ይህ ሁሉ መልካም እና የሚያስመሰግን ነበር። ከዚህ ፈሪሳዊ ጽድቅ በታች የሆኑ ሰዎች ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ነው፤ ሆኖም ግን እሱ አልተወደደም (አልተቀበለም)፤ ለምንስ አልተቀበለም? ወደ ቤተ መቅደስ የሄደው ለመጸለይ ነበር፤ ነገር ግን በራሱና በራሱ መልካምነት ተሞልቶ ነበር፤ የእግዚአብሔርን ሞገስና ጸጋ መጠየቅ እንደሚያስፈልገው አላሰበም። እንግዲህ ለእግዚአብሔር ኩሩ አምልኮ (ጸሎት) ከማቅረብና ሌሎችንም ከመናቅ እንጠንቀቅ።

የቀረጥ ሰብሳቢው ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎት በትህትና፣ በኃጢአት ንስሐና ወደ እግዚአብሔር ባለው ናፍቆት የተሞላ ነበር። ጸሎቱ አጭር ቢሆንም ዓላማ ያለው ነበር፤ እንዲህም አለ፦ ‘አምላክ ሆይ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ።’ ይህ አጭር ጸሎት እንደተመለሰ ጸሎት ተመዝግቦልን በመገኘቱና፣ የጸለየውም ወደ ቤቱ ጸድቆ እንደሄደ እርግጠኞች በመሆናችን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ እኛም እንደ እርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከጸለይነው እንዲሁ እንጸድቃለንና። እርሱ በተፈጥሮ፣ በተግባርም ኃጢአተኛ መሆኑንና በእግዚአብሔር ፊት ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል። ጥገኝነቱ በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ብቻ ነበር፤ በዚያ ላይ ብቻም ተማምኖ ነበር። የእግዚአብሔር ክብርም ትዕቢተኞችን መቃወም፣ ለትሑታንም ጸጋን መስጠት ነው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6