1እግዚአብሔር የጽዮንን ሴት ልጅ፣ በቍጣው ደመና እንዴት ጋረዳት! ከሰማይ ወደ ምድር፣ የእስራኤልን ክብር ወርውሮ ጣለው፤ በቍጣው ቀን፣ የእግሩን መቀመጫ አላስታወሰም።
2የያዕቆብን መኖሪያ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ያለ ርኅራኄ ዋጣቸው፤ የይሁዳን ሴት ልጅ ምሽጎች፣ በቍጣው አፈረሳቸው፤ መንግሥቷንና መሳፍንቷን፣ በማዋረድ ወደ ምድር ጣላቸው።
3በጽኑ ቍጣው፣ የእስራኤልን ቀንድ ሁሉ ሰበረ፤ ጠላት በተቃረበ ጊዜ፣ ቀኝ እጁን ወደ ኋላ መለሰ፤ በዙሪያው ያለውን ሁሉ እንደሚበላ እሳት፣ በያዕቆብ ላይ የእሳት ነበልባል ነደደ።
4እንደ ጠላት ቀስቱን ገተረ፤ ቀኝ እጁ ተዘጋጅታለች፤ ለዐይን ደስ የሚያሰኙትን ሁሉ፤ እንደ ጠላት ዐረዳቸው፤ በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳን ላይ፣ ቍጣውን እንደ እሳት አፈሰሰ።
5እግዚአብሔር እንደ ጠላት ሆነ፤ እስራኤልንም ዋጠ፤ ቤተ መንግሥቶቿን ሁሉ ዋጠ፤ ምሽጎቿን አፈራረሰ፤ በይሁዳ ሴት ልጅ፣ ለቅሶንና ሰቈቃን አበዛ።
6ማደሪያውን እንደ አትክልት ስፍራ ባዶ አደረገ፤ መሰብሰቢያ ስፍራውን አፈረሰ፤ እግዚአብሔር ጽዮንን፣ ዓመት በዓላቶቿንና ሰንበታቷን እንድትረሳ አደረጋት፤ በጽኑ ቍጣው፣ ንጉሡንና ካህኑን እጅግ ናቀ።
7እግዚአብሔር መሠዊያውን ናቀ፤ መቅደሱንም ተወ፤ የቤተ መንግሥቶቿን ቅጥሮች፣ ለጠላት አሳልፎ ሰጠ፤ በዓመት በዓል ቀን እንደሚደረገው በእግዚአብሔር ቤት በኀይል ጮኹ።
8በጽዮን ሴት ልጅ ዙሪያ ያለውን ቅጥር፣ እግዚአብሔር ለማፍረስ ወሰነ፤ የመለኪያ ገመድ ዘረጋ፤ ከማጥፋትም እጆቹን አልሰበሰበም፤ ምሽጎችና ቅጥሮች እንዲያለቅሱ አደረገ፤ በአንድነትም ጠፉ።
9በሮቿ ወደ ምድር ሰመጡ፤ የብረት መወርወሪያዎቻቸውን ሰባበረ፤ አጠፋቸውም፤ ንጉሥዋና መሳፍንቶቿ በአሕዛብ መካከል ተማርከው ተሰደዋል፤ ሕጉ ከእንግዲህ አይኖርም፤ ነቢያቶቿም ከእንግዲህ፣ ከእግዚአብሔር ራእይ አያገኙም።
10የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች፣ በምድር ላይ በዝምታ ተቀምጠዋል፤ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ፤ ማቅም ለበሱ፤ የኢየሩሳሌም ወጣት ሴቶች፣ ራሳቸውን ወደ ምድር ዝቅ አደረጉ።
11ዐይኔ በለቅሶ ደከመ፤ ነፍሴ በውስጤ ተሠቃየች፤ ልቤም በሐዘን ፈሰሰች፣ በከተማዪቱ መንገዶች ላይ፣ ሕዝቤ ተደምስሰዋልና፤ ልጆችና ሕፃናት ደክመዋልና።
12በከተማዪቱ መንገዶች ላይ፣ እንደ ቈሰሉ ሰዎች ሲደክሙ፣ በእናታቸው ክንድ ላይ፣ ነፍሳቸው በመውጣት ላይ ሳለች፣ “እንጀራና የወይን ጠጅ የት አለ?” እያሉ እናቶቻቸውን ይጠይቃሉ።
13የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፤ ስላንቺ ምን ማለት እችላለሁ? ከምንስ ጋር አወዳድርሻለሁ? ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፤ አጽናናሽ ዘንድ፣ በምን ልመስልሽ እችላለሁ? ቍስልሽ እንደ ባሕር ጥልቅ ነው፤ ማንስ ሊፈውስሽ ይችላል?
14የነቢያቶችሽ ራእይ፣ ሐሰትና ከንቱ ነው፤ ምርኮኛነትሽን ለማስቀረት፣ ኀጢአትሽን አይገልጡም። የሚሰጡሽም የትንቢት ቃል፣ የሚያሳስትና ከመንገድ የሚያወጣ ነው።
15በአጠገብሽ የሚያልፉ ሁሉ፣ እጃቸውን ያጨበጭቡብሻል፤ “የውበት መደምደሚያ፣ የምድር ሁሉ ደስታ፣ የተባለች ከተማ ይህች ናትን?” እያሉ ራሳቸውን በመነቅነቅ፣ በኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ላይ ያሾፋሉ።
16ጠላቶችሽ ሁሉ በአንድ ላይ፣ አፋቸውን በኀይል ከፈቱ፤ ጥርሳቸውን እያፏጩ አሾፉ፤ እንዲህም አሉ፤ “ውጠናታል፤ የናፈቅነው ጊዜ ይህ ነበር፤ ኖረንም ልናየው በቃን።”
17እግዚአብሔር ያሰበውን አደረገ፤ ከረዥም ጊዜ በፊት የተናገረውን፣ ቃሉን ፈጸመ፤ ያለ ርኅራኄ አፈረሰሽ፤ ጠላት በሥቃይሽ ላይ እንዲደሰት፣ የጠላትሽንም ቀንድ ከፍ ከፍ አደረገ።
18የሕዝቡ ልብ፣ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። የጽዮን ሴት ልጅ ቅጥር ሆይ፤ ቀንና ሌሊት፣ እንባሽ እንደ ወንዝ ይፍሰስ፤ ለራስሽ ዕረፍትን አትስጪ፣ ዐይኖችሽ ከማንባት አያቋርጡ።
19የሌሊቱ ሰዓት ሲጀምር፣ ተነሺ በሌሊት ጩኺ፤ በእግዚአብሔር ፊት፣ ልብሽን እንደ ውሃ አፍስሺ፤ በየመንገዱ ዳር ላይ፣ በራብ ስለወደቁት፣ ስለ ልጆችሽ ሕይወት፣ እጆችሽን ወደ እርሱ አንሺ።
20አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ እይ፤ ተመልከትም፤ በማን ላይ እንዲህ አድርገህ ታውቃለህ? በውኑ እናቶች ሕፃኖቻቸውን፣ ተንከባክበው ያሳደጓቸውን ልጆች ይብሉን? ካህኑና ነቢዩስ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ይገደሉን?
21በየመንገዱ ዐቧራ ላይ፣ ወጣትና ሽማግሌ በአንድነት ወደቁ፤ ወይዛዝርቴና ጐበዛዝቴ፣ በሰይፍ ተገደሉ፤ በቍጣህ ቀን ገደልሃቸው፤ ያለ ርኅራኄም ዐረድሃቸው።
22“በበዓል ቀን ለግብዣ እንደምትጠራ፣ ሽብርን ከየአቅጣጫው በእኔ ላይ ጠራህ፤ በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን፣ ማንም አላመለጠም ወይም አልተረፈም፤ የተንከባከብኋቸውንና ያሳደግኋቸውን፣ ጠላቴ አጠፋብኝ።”