1“በውኑ አዞውን በመቃጥን ታወጣለህን? ምላሱንስ በገመድ ታስረዋለህን?
2ወይስ ስናጋ በአፍንጫው ታደርጋለህን? ወይስ በችንካር ጕንጩን ትበሳለህን?
3በውኑ ወደ አንተ እጅግ ይለምናልን? በጣፈጠስ ቃል ይናገርሃልን?
4በውኑ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን ይገባልን? ወይስ ለዘላለም ባሪያ ታደርገዋለህን?
5ከወፍ ጋር እንደምትጫወት ከእርሱ ጋር ትጫወታለህን? ወይስ ለሴት ባሪያዎችህ ታስረዋለህን?
6አጥማጆች በእርሱ ይከራከራሉን? ወይስ ነጋዴዎች ያካፍሉታልን?
7በውኑ ቁርበቱን በጭሬ፥ ራሱንስ በዓሣ ጦር ትሞላዋለህን?
8እጅህን በላዩ ጫን፤ ሰልፉን አስብ፥ እንግዲህም አትድገም።
9እነሆ፥ ተስፋው ከንቱ ነው፤ ያየው ሁሉ ስንኳ በፊቱ ይዋረዳል።
10ያንቀሳቅሰውም ዘንድ የሚደፍር የለም፤ እንግዲህ በፊቴ መቆም የሚችል ማን ነው?
11እመልስለትስ ዘንድ መጀመሪያ የሰጠኝ ማን ነው? ከሰማይ ሁሉ በታች ያለው ገንዘቤ ነው።
12“ስለ አካላቱና ስለ ብርቱ ኃይሉ፥ ስለ መልካም ሰውነቱ ዝም አልልም።
13የውጪ ልብሱን ማን ይገፋል? በጥንድ መንጋጋውስ ውስጥ ማን ይገባል?
14የፊቱንስ ደጆች የሚከፍት ማን ነው? በጥርሶቹ ዙሪያ ግርማ አለ።
15ቅርፊቶቹ ጠንካራ ስለ ሆኑ እርሱ ትዕቢተኛ ነው፤ በጠባብ ማተሚያ እንደ ታተሙ ናቸው።
16እርስ በርሳቸው የተቀራረቡ ናቸውና፡ ነፋስ በመካከላቸው መግባት አይችልም።
17እርስ በርሳቸው የተገጣጠሙ ናቸው፤ እስከማይለያዩም ድረስ ተያይዘዋል።
18እንጥሽታው ብልጭታ ያወጣል፥ ዓይኖቹም እንደ ወገግታ ናቸው።
19ከአፉ ፋናዎች ይወጣሉ፥ የእሳትም ፍንጣሪ ይረጫል።
20እንደ ፈላ ድስትና እንደሚቃጠል ሸምበቆ፡ ከአንፍንጫው ጢስ ይወጣል።
21እስትንፋሱ ከሰልን ታቃጥላለች፥ ነበልባልም ከአፉ ይወጣል።
22በአንገቱ ኃይል ታድራለች፤ ግርማ በፊቱ ይዘፍናል።
23የሥጋውም ቅርፊት የተጣበቀ ነው፤ እስከማይንቀሳቀሱም ድረስ በእርሱ ላይ ጸንተዋል።
24ልቡ እንደ ድንጋይ የደነደነ ነው፤ እንደ ወፍጮ ድንጋይ የጸና ነው።
25በተነሣ ጊዜ ኃያላን ይፈራሉ፤ ከድንጋጤም የተነሣ ያብዳሉ።
26ሰይፍና ጦር፥ ፍላጻና መውጊያም ቢያገኙት አያሸንፉትም።
27ብረትን እንደ ገለባ፥ ናስንም እንደ ነቀዘ እንጨት ይቈጥራቸዋል።
28ፍላጻ ሊያባርረው አይችልም፤ የወንጭፍም ድንጋዮች እንደ ገለባ ይሆኑለታል።
29በሎታውን እንደ ገለባ ይቈጥረዋል፤ ሰላጢኑም ሲሰበቅ ይስቃል።
30ታቹ እንደ ስለታም ገል ነው፤ እንደ መዳመጫም በጭቃ ላይ ያልፋል።
31ቀላዩን እንደ ድስት ያፈላዋል፤ ባሕሩንም እንደ ሽቱ ምንቸት ያደርገዋል።
32በስተ ኋላው ብሩህ መንገድን ያበራል፤ ቀላዩም ሽበት ይመስላል።
33ያለ ፍርሃት የተፈጠረ፥ እንደ እርሱ ያለ በምድር ላይ የለም።
34ከፍ ያለውን ሁሉ ይመለከታል፤ በትዕቢተኞችም ሁሉ ላይ ንጉሥ ነው።”